በሃገረ ስብከቱ ስራአስኪያጅ ግድያ 12 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ታስረዋል፤ ዲያቆናትም፤ ካህናትም አሉበት የወልዳ ዱከ ማህበር ሰብሳቢም አሉበት

” የተጠረጠሩ 21 ሰዎች አሉ። የኦሮሚያ ጸጥታ ዘርፍም አረጋግጦ አስቀምጧል፤ ደብዳቤም አለ ” – የሆሮጉዱሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት

➡️ ” 12 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ታስረዋል፤ ዲያቆናትም፤ ካህናትም አሉበት። የወልዳ ዱከ ማህበር ሰብሳቢም አሉበት ” – ቤተክርስቲያኗ

ከሳምንት በፊት በተገደሉት የሆሮጉድሩ ወለጋ ሀገረ ስብሰት ዋና ስራ አስኪያጅ በመላከኤዶም ቀሲስ ዱጉማ ግድያ 21 ሰዎች መጠርጠራቸውን፣ ከእነዚህም መካከል ወደ 12 የሚሆኑት መያዛቸውን ሀገረ ስብከቱና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

የሆሮጉድሩ ወለጋ ሀገረስብከት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምን አለ ?

ስለጉዳዩ የጠየቅነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሆሮጉድሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጠው ቃል፣ ” የተጠረጠሩ 21 ሰዎች አሉ። የኦሮሚያ ጸጥታ ዘርፍም አረጋግጦ አስቀምጧል፤ ደብዳቤም አለ ” ብሏል።

ለደኀንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን አንድ የሀገረ ስብከቱ አመራር፣ ” ሟቹ መጀመሪያ አመልክተዋል፤ በፊትም ሲጣሉ የነበረው ‘በኦሮሚያ ሲኖዶስና በኢትዮጵያ’ ተብሎ እንዲሞቱ ብዙ ትኩረት ሲያደርጉ የነበሩት እነኝህ ሰዎችን ነው ” ያሉ ሲሆን፣ ሟቹ ይህን መናገራቸውን “መንግስትም ያውቃል” ሲሉ ገልጸዋል።

“እሳቸው መጀመሪያም ‘እኔ ከሞትኩ’ ብለው ማመልከቻ አስገብተው 21 ሰዎችን ጠቅሰው ‘የሀገሩ ጸር ስለሆኑ ክትትል እንድታደርጉ’ ብለው ለጸጥታ ዘርፍም ለሀገረ ስብከቱም ደብዳቤ ተጽፏል። ደብዳቤው ያልገባበት ቦታ የለም በእጃችንም አለ” ነው ያሉት።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በቁጥጥር ስር የዋሉ አሉ? ” ተጠጣርዎቹ የቤተክርስቲያን ውስጥ የሚሰሩ ካህናትና ዲያቆናት አሉበት ” መባሉስ ትክክል ነው ? ለሚለው የቲክቫህ ኢትዮጵያ ጥያቄም፣ “6 ሰዎች ተይዘዋል” የሚል ምላሽ ሰጥተው፣ “ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የቤተክስርስቲያን አገልጋዮች አሉበት” መባሉን በተመለከተ ግን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ቤተክርስቲያኗ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምን አለች ?

ቲክቫህ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ማብራሪያ የጠየቃቸው አንድ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አመራር፣ ” በግድያው 12 የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ታስረዋል፤ ዲያቆናትም፤ ካህናትም አሉበት። ዞሮ ዞሮ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉ ናቸው። የወልዳ ዱከ ማህበር ሰብሳቢም አሉበት’ የሚል መረጃ አጣርቻለሁ” ብለዋል።

ታሰሩ የተባሉትም በሆሮጉድሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መላከ ኤዶም ቀሲስ ዱጉማ ግድያ ተጠርጥረው መሆኑን እኝሁ አካል ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

የካህናቱን ግድያ በተመለከተም፣ “የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እጅ አለበት፤ ሟች ዋና ስራ አስኪያጁም ከሞትኩ ገዳዮቸ እነዚህ ናቸው ብለው ስም ዝርዝራቸውን ጭምር ተናግረው ነበር” የሚል መረጃ ሰሞኑን ማህበራዊ ሚዲያው በሰፊው ተሰራጭቷል።

ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ምላሽ የጠየቃት ቤተክርስቲያኗ፣ ” በግድያው እጃቸው ያለበት ሰዎች አሉ ” በሚል ” ሚዲያው ላይ እየወጣ ያለው ነገር ትክክል ነው ” ብለዋል። ” ቤተክስርስቲያኗም ተጨማሪ ማጣራት አድርጋ የሆነ ማለቷ አይቀርም ” ሲሉም ገልጸዋል።

ከግድያው ጋር በተያያዘ ስሙ የተነሳው “በኢትየጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአፋር ኦሮሞ መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት በ2004 የተመሰረተው” ወልዳ ዱከ ቡኦታ ጠቅላላ ማህበር በበኩሉ፣ በማህበሩ አባል መላከኤዶም ቀሲስ ዱጉማ እንዲሁም በቀሲስ ደሳለኝ ነሞምሳ ግድያን ማውገዙን አስተውሶ፣ ይሁን እንጅ “የስም ማጥፋት ዘመቻ በሰፊው ተከፍቶብኛል” ሲል ባወጣው መግለጫ ወቅሷል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ የኦሮሚያ ክልል እና ሆሮጉዱሩ ወለጋ የጸጥታ አካላት ስለጉዳዩ ያላቸውን ሀሳብ ለማካተት ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው ያልተሳካ ሲሆን፤ ፈቃደኞች ከሆኑ በሩ ክፍት ነው።