የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (ዩኤንኤችሲአር) በጋምቤላ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስ ተከትሎ ለስደተኞች የሚያቀርበውን አገልግሎት መቋረጡን ገለጸ።
ድርጅቱ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ በክልሉ በተከሰተው ግጭት የተነሳ ለስደተኞች የሚደርስ የምግብ እና የውሃ አቅርቦት ለጊዜው መቋረጡን ገልጿል።
በጋምቤላ ክልል ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ የንብረት መውደም እና የአካል ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 14/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የተቋረጠውን የእርዳታ አቅርቦት ለማስቀጠል ጥረት እያደረገ መሆኑንም ጠቅሷል።
ዩኤንኤችሲአር በክልሉ የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋት ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ “ስደተኞች ላይ ያተኮረ” ሐሰተኛ መረጃ መሠራጨቱን እና ይህም እንዳሳሰበው አስታውቋል።
ድርጅቱ ሁኔታው በፍጥነት ትኩረት ካልተሰጠው “ውጥረትን ያባብሳል” ሲል ስጋቱን ገልጿል።
ድርጅቱ ለተፈጠረው አለመረጋጋት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ አቅርቦ “ማንኛውም ሰው ስደተኞች እና ስደተኛ ተቀባይ ማኅበረሰብ ላይ ከሚሰነዘሩ የጥላቻ ንግግር እንዲታቀብ” ጠይቋል።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ከ483 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያ ይኖራሉ።
ወደ 450 ሺህ የሚጠጉ ከደቡብ ሱዳን ግጭት ሸሽተው የመጡ ስደተኞች በጋምቤላ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይኖራሉ።
መጠለያ ጣቢያዎቹ በርካታ ስደተኞችን የያዙ ቢሆንም በደቡብ ሱዳን ባለፈው ዓመት ያገረሸው ግጭት በርካቶች ወደ ጋምቤላ እንዲሰደዱ አድርጓል።
በጥቅምት ወር በደቡብ ሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአገሪቱ በታጠቁ ኃይሎች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች፣ የፖለቲካ እስር እና የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች ከቅርብ ወራት ወዲህ መጨመራቸውን ገልጿል።
ብጥብጡ መባባስ የጀመረው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻርን በቁጥጥር ስር ባዋለበት ወቅት ነው።
የፎቶው ባለመብት, Gambella Press Secretariat Office
የመከላከያ እና ፌደራል ፀጥታ አካላት መሰማራት
በጋምቤላ ክልል ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የመከላከያ እና የፌደራል ፀጥታ አካላት መሰማራታቸውን ኢሰመኮ ሰኞ ዕለት ለቢቢሲ ገልጿል።
ኢሰመኮ በክልሉ በሰዎች በሕይወት መኖርን ጨምሮ ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይደርሱ ለመከላከል በቂ የፀጥታ አካላት “በአስቸኳይ” እንዲሰማሩ የጠየቀው እሁድ ታኅሣሥ 12/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነበር።
በኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ክፍል ከፍተኛ ዳይሬክተር የሆኑት በዳሳ ለሜሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “አሁን በከተማው እና በዙሪያው በቂ የፀጥታ አካላት አሉ። የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ የከተማው ፀጥታ እንዲረጋጋ አድርገዋል” ብለዋል።
ኢሰመኮ በጋምቤላ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በክልሉ ነዋሪዎች ሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት በተመለከተ ባወጣው መግለጫ በክልሉ ውስጥ ባሉት ኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ጋምቤላ ወረዳ እና በጋምቤላ ከተማ ከኅዳር 28 ጀምሮ የተፈጠሩ ግጭቶችን እየተከታተለ እንደሚገኝ ገልጿል።
የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ አዛዥ የነበሩት የዋና ኢንስፔክተር ኡሞድ ኡጅሉን መገደል ተከትሎ በጋምቤላ ከተማ እና በአካባቢው ባሉት ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር ኢሰመኮ በመግለጫው ጠቅሷል።
ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭትና የፀጥታ መደፍረስ ተከትሎ “የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ የሰዎችን እና የመጓጓዣ አማራጮችን እንቅስቃሴ የሚገድብ የሰዓት እላፊ በክልሉ መንግሥት መጣሉን፤ ባንኮችን እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎት ማቋረጣቸውን” ጨምሮ ገልጿል።
ዋና ዳይሬክተሩ አቶ በዳሳ ለሜሳ ለቢቢሲ ዛሬ ሰኞ ታኅሣሥ 13 እንደተናገሩት መንግሥታዊ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ እንዲሁም የንግድ ተቋማት እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በመግለጫው ላይ በጋምቤላ ክልል በተፈጠረው ግጭት እና የፀጥታ መደፍረስ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት መድረሱን ገልጾ ነበር።
ቢቢሲ በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳትን በተመለከተ ለአቶ በዳሳ ጥያቄ ያቀረበላቸው ሲሆን፣ በግጭቱ የሞቱ እና የቆሰሉ ሰዎች ምን ያህል እንደሆኑ ለመናገር “የምርመራ ሥራዎች” መከናወን ስላለባቸው አሁን መናገር እንደማይችሉ ተናግረዋል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በመግለጫው ላይ በጋምቤላ ክልል የሚከሰቱ ግጭቶች እና የሰላም መደፍረሶች በክልሉ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል የሚደረጉ ጥረቶችን እና እርምጃዎችን እየተፈታተኑ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ያቀረባቸውን እና ከዚህ ቀደም ለፌዴራሉ እና ለክልሉ መንግሥታት የሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦች በተሟላ ሁኔታ እንዲፈጸሙ ማድረግ እንደሚገባ ኮሚሽነሩ የተናገሩ ሲሆን፣ ዋና ዳይሬክተሩም የክትትል ሥራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለሳምንታት የቆየው የጋምቤላ አለመረጋጋት
የጋምቤላ ክልል አስተዳደር ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ባወጣው መግለጫ “የክልሉ ሕዝብ ሰላም እንቅልፍ የሚነሳቸው እና ግጭት እና የሰው ሞት የሚያስደስታቸው” ያላቸው በስም ያልጠቀሳቸው ኃይሎች የጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ወረዳዎች ትርምስ ፈጥረዋል ብሎ ነበር።
የክልሉ መንግሥት ባወጣው በዚህ መግለጫ ላይ እነዚህ ኃይሎች “ሰዎችን በመግደል፣ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት በማድረስ እና ሕይወት እንዲጠፋ በማድረግ፣ የፀጥታ አካላትን እና አመራርን ዒላማ በማድረግ” የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረጋቸውን ገልጿል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ አንድ የባንክ ꬅሥራ አስኪያጅ በመቀጠልም የጋምቤላ ከተማ ፖሊስ ጽሕፈት ቤት አዛዥ የነበሩት ዋና ኢንስፔክተር ኡመድ ኡጁሉ ተገድለዋል።
የጋምቤላ ፖሊስ አዛዥ የተገደሉት የባንክ ሥራ አስኪያጁ ከተገደሉ ከቀናት በኋላ ነው።
ቢቢሲ በወቅቱ ያነጋገራቸው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ከዚያ በኋላ የአካባቢው ወጣቶች ተነስተው “ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት” እንደፈጸሙ ተናግረዋል።
“ግጭቱ ተነስቶ ወደ ብዙ አካባቢዎች ተስፈፍቷል” ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
ጥቃት አድራሾቹ “በተደራጀ ሁኔታ” የሚንቀሳቀሱ አለመሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ “በመጣው ለውጥ ደስ ያላላቸው” እንዲሁም “አንዳንዶቹም ከአሜሪካ ገንዘብ የሚላክላቸው ተራ ሰዎች ናቸው” ብለው ነበር።
ለጥቃቱ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ከታጣቂዎች ጋር “በውስጥ በተቀናጀ መንገድ የሚገናኙ ከሆነ አናውቅም” ሲሉም አክለዋል።
ይህንን በተከታታይ የሚፈጸም ጥቃት ማስቆም ያልተቻለው ጥቃት አድራሾቹ “የተደራጁ እና በአንድ የተወሰነ አካባቢ” ላይ ያሉ አለመሆናቸውን እና “በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ” መሆኑን እንደምክንያት ጠቅሰዋል።
ኢሰመኮ በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን በዘላቂነት ለማስቆም፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እና ወደፊት ተመሳሳይ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ለመከላከል የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥታት ተገቢ እርምጃዎችን እንዲወስዱም አሳስቧል።
በክልሉ የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስ ለመቆጣጠር የጋምቤላ ከተማ አስተዳደር ከኅዳር 30/2018 ዓ.ም. አንስቶ ከፀጥታ አካላት ውጪ ማንኛውም ተሽከርካሪ እና ሰው ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ የሚከልክል የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሏል።
በክልሉ ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ በሰዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት እና ምን ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ እስካሁን በይፋ የታወቀ ነገር የለም።