
በትግራይ ክልል በሰሜናዊ ምዕራብ አካባቢ ካሉት የተፈናቃይ ካምፖች መካከል አንዱ በሆነው ሕጻጽ በርካቶች በረሃብ ውስጥ መሆናቸውን ለቢቢሲ ትግርኛ ተናገሩ።
ተፈናቃዮቹ በእርዳታ የሚደርሳቸው ምግብ ድጋፍ በቂ ካለመሆኑም በላይ ከፍተኛ የጥራት ችግር እንዳለበት ገልጸዋል።
በምዕራብ ትግራይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እጥረት ምክንያት “በረሃብ እና በበሽታ” የመጠቃት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተናግረዋል።
ከአስር ሺህ በላይ ተፈናቃዮች በሚኖሩበት የሕጻጽ መጠለያ ውስጥ በርካታ አዛውንቶች፣ ነፍሰ ጡር እናቶች እና ሕጻናት በምግብ እና በሕክምና እጦት እየተሰቃዩ መሆኑን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
የሕጻጽ የተፈናቃዮች ማዕከል አስተባባሪ ቄስ አብርሃ አርአያ እንዳሉት ቢያንስ 300 ሰዎች ባለፉት ስድስት ወራት የእርዳታ እህል አላገኙም።
በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የሚገኙት አንድ እናት ለቢቢሲ ትግርኛ ስለሁኔታው ሲያስረዱ “አረጋውያን አሉ፤ ጉድ ነው የምናየው። አንዳንድ ለነፍሴ ያለ የሚያመጣልን እንጀራም ደርቆ እርሱም አይበላም። በውሃ ነክረው ፈትፍተው ለመብላት ይሞክራሉ” ብለዋል።
የትግራይ ጦረነት ሲቀሰቀስ ቤተሰቦቻቸው ተበታትነው ወደ ሱዳን መሰደዳቸውን የሚናገሩት እኚህ እናት አሁን ብቻቸውን መቅረታቸውን ይናገራሉ።
“እዚህ ሰው ሁሉ በረሃብ አንጀቱ ተጣብቋል” ያሉት ተፈናቃይዋ “ዋናው ችግር ምግብ የሚባል ነገር የለም። የሚሰጡንም እህል የሚሆን አይደለም። ባለፉት ስድስት ወራት የሰጡን እህል፣ እህል የሚባል አይደለም” ሲሉ የሚሰጣቸው የእርዳታ እህል ጥራት ችግር አንዳለበት ያስረዳሉ።
. . .ያቺንም የምትሰጠውን የማያገኝ አለ። ማሽላው ራሱ የተበላሸ ነው፤ ብዙ ቆሻሻ አለው። ታጥቦ ራሱ እህል መሆን አይችልም። ያቺም የተበላሸች እህል ስንት ነፍሰ ጡር፣ ስንት አረጋውያን ስንት አራስ አያገኛትም” ሲሉ ያለውን ችግር አስረድተዋል።
“እስከ ዛሬ በሕይወት መቆየታችን ራሱ ተመስገን ነው የሚባለው። ከአሁን በኋላ ደግሞ ምን እንደምንሆን አናውቅም።”
በትግራይ ክልል በመቀለ፣ በሽረ፣ በተምቤን፣ በአቢ አዲ፣ በሰሜን ምዕራብ አካባቢ ደግሞ ሰለህለሃ በአጠቃላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የክልሉ መንግሥት ይገልጻል።
በሕጻጽ መጠለያ ውስጥ የተፈናቃዮች አስተባባሪ የሆኑት ቄስ አብርሃ አርአያ በበኩላቸው በካምፑ ውስጥ ዘግይተው የመጡ አረጋውያን መኖራቸውን ገልጸው እነርሱ አሁን ለችግር መጋለጣቸውን ያስረዳሉ።
እነዚህ በዕድሜ የገፉ ተፈናቃዮች “እህል ውሃ ቢያገኙም ጧሪ ስለሌላቸው ከጤና ሁኔታም አንጻር ያለባቸው ችግር የበረታ ነው” ማለታቸውን ቢቢሲ ትግርኛ ዘግቧል።
የረሃብ ችግሩ በተለያዩ አካባቢዎች ቢከሰትም የሕጻጽ አካበቢ የተለየ የሚያደርገው “አረጋውያን የሚገኙበት ካምፕ ስለሆነ ነው” ሲሉ አስተባባሪው ተናግረዋል።
የካምፑ አስተባባሪ ብዙዎች ታምመው እንዳሉ ገልጸው በቅርብ ጊዜ ውስጥ “አምስት ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን” ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ከ2014 ዓ.ም ወዲህ “330 ሰዎችን ቀብረናል” ያሉት አስተባባሪው፤ ሰዎቹ የሞቱት በረሃብ ምክንያት መሆን አለመሆኑን አላስረዱም።
በአሁኑ ወቅት በሕጻጽ ካምፕ ወደ 14 ሺህ ሰዎች እርዳታ የሚያገኙ ቢሆንም ባለፉት ወራት 300 የሚሆኑት ምንም ዓይነት እርዳታ አለማግኘታቸውን አስተባባሪው ጨምረው ተናግረዋል።
የሚሰጣቸው እህል ማሽላ መሆኑን የሚናገሩት አስተባባሪው፣ ማሽላውም የተበላሸ እንደሆነ እና ሌላ ተጨማሪ ገንቢ ምግብ አንደማያገኙ፣ ሕክምናም ሆነ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዳለባቸው ገልጸዋል።
“ለስድስት ወራት እህል የማያገኝ ሰው አለ። የሚያገኘውም አንድ ወይንም ሁለት ኪሎ ነው። የሚመጣውም እህል ጥራት የሌለው ነው። አይጥም የማትበላው እህል ነው የሚደርሰን። ድረሱልን ብለን ጥሪ አድርገን የሚረዳን አላገኘንም።”
የትግራይ የሲቪክ ማኅበራት ሕብረት ጥምረት ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ይካሎ ወልዱ በክልሉ 90 የሚሆኑ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መኖራቸውን ገልፀው፣ በሕጻጽ ያለው የረሃብ ችግር የተባባሰው ከባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ መሆኑን ያስረዳሉ።
በመጠለያ ጣቢያዎቹ ውስጥ “ከፍተኛ የሆነ የምግብ እንዲሁም የእርዳታ እጥረት አለ” ያሉት ዶ/ር ይካሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከክልሉ ለቅቀው እየወጡ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
ዶ/ር ይካሎ አክለውም በክልሉ ለሚገኙ የተፈናቀሉ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች እና መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ የበለጠ ማኅበረሰቡ የሚሰጠው እንደሚበልጥ አስረድተዋል።
በሕጻጽ የተፈናቃዮች መጠለያ ብቻ ከ14,000 እስከ 16,000 የሚደርሱ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ ተንቀሳቅሰው “መለመን የማይችሉ እናቶች፣ ሕጻናት እና አዛውንቶች የበለጠ ተጎጂ “መሆናቸውን ገልጸዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግደው አዘናው በበኩላቸው ይህንን የተፈናቃዮች የረሃብ ችግር በተለያዩ የተፈናቃዮች ካምፕ እየታየ መሆኑን ይናገራሉ።
ችግሩ እንዲበረታ ያደረገው ተፈናቃዮች ለአምስት ተከታታይ ክረምት በዚህ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ማሳለፋቸው መሆኑን የጠቀሱት አስተዳዳሪው፣ በቂ እርዳታም እንደማያገኙ ይገልጻሉ።
ለአንድ ሰው የሚሰጠው እርዳታ በወር 15 ኪሎ ማሽላ ነው የሚሉት አቶ ግደው ይህም በቂ አንዳልሆነ እና ደኅንነቱ የተረጋገጠ ባለመሆኑ ተነሳ ችግር ማጋጠሙን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ያለባቸው ችግር ከተነገረ በኋላ የተለያዩ ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ እየተረባረቡ እንደሚገኝ የዞኑ አስተዳዳሪ ጨምረው ገልጸዋል።
በሕጻጽ የመጠለያ ጣቢያ አረጋውያን የሚበዙበት መሆኑ፣ ተፈናቃዮች ሲመጡ ዘግይተው የመጡ አረጋውያን መኖራቸው እና እነርሱ የሚያግዛቸው የሚጦራቸው ባለመኖሩ ችግሩን የበለጠ እንዲከፋ ማድረጉን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
ይህንን ችግር ለመፍታት እየተንቀሳቀስን ነው የሚሉት አስተዳዳሪው ሰኞ ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም. ከ400 ኪሎ በላይ ዱቄት ከሽሬ አካባቢ ወደ ሕጻጽ መጠለያ ካምፕ መወሰዱን ጨምረው አስታውቀዋል።
ግለሰቦች እርዳታ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን እና የባንክ አካውንት ተከፍቶም እርዳታ ማሰባሰብ መጀመሩን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
የራያ ዩኒቨርስቲም የተለያዩ እርዳታዎችን በመያዝ ወደ አካባቢው እንደተጓዘ የተናገሩት አቶ ግደው፣ በሽረ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች እንዲሁ በማኅበራዊ ሚዲያ እርዳታ ለማሰባሰብ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል በተካሄደው ደም አፋሳሽ ግጭት ከሦስት ዓመታት በፊት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢቆምም አሁንም በሺህዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለስ አልቻሉም።
ሕጻፍ የተፈናቃዮች ካምፕ ቀደም ሲል የኤርትራ ስደተኞች ማቆያ ስፍራ የነበረ ሲሆን፣ በትግራይ ከተካሄደው በኋላ ግን ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች መጠለያ ሆኗል።