እስራኤል በሐማስ የተፈጸመባትን ጥቃት ተከትሎ በጋዛ ለሁለት ዓመታት ያካሄደችው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻን በተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያበቃ፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና በከፍተኛ ሁኔታ የወደመችውን ጋዛን መልሶ ለመገንባት ዕቅድ መቅረቡ ይታወቃል።
በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀረበው እና በተበባሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ተቀባይነት ያገኘው ባለ20 ነጥብ የሰላም ዕቅድ ከጥምቅት መጀመሪያ አንስቶ ተግባራዊ በመሆኑ በጋዛ የሚካሄደው ጥቃት ጋብ ብሏል።
በሰላም ዕቅዱ በጋዛ ውስጥ የደኅንነት ጥበቃ የሚያደርግ እና የተኩስ አቁም ስምምነቱን የሚቆጣጠር ዓለም አቀፍ አረጋጊ ኃይል (አይኤስኤፍ) ተቋቁሞ እንደሚሰማራ ተጠቅሷል።
ትራምፕ ያቀረቡት 20 ነጥቦችን በያዘው የሰላም ዕቅድ ውስጥ በ15ኛ ተራ ቁጥር ላይ የሰፈረው ሐሳብ “አሜሪካ ከአረብ እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመሥራት ጊዜያዊ ዓለም አቀፍ አረጋጊ ኃይል (አይኤስኤፍ) በማዋቀር በአስቸኳይ ጋዛ ውስጥ እንዲሰማራ ይደረጋል” ይላል።
ይህ ኃይል ከዮርዳኖስ እና ከግብፅ ጋር በመመካከር በጋዛ ውስጥ የሚሰማራውን የፖሊስ ኃይል አባላትን አጣርቶ በመመልመል ሥልጠና ይሰጣል፣ በጥምረትም ከግብፅ እና ከእስራኤል ጋር በመሆን የድንበር አካባቢ ደኅንነትን የመጠበቅ ኃላፊነት ይሰጠዋል።
እንዲሁም ጋዛ ሰርጥን ከወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ነጻ ማድረግ፣ ሐማስን ትጥቅ ማስፈታት እንዲሁም በጣም አስፈላጊ የሆነውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት የተሳካ እንዲሆን ማመቻቸት የሚሰማራው ኃይል ኃላፊነት እንደሚሆን ተነግሯል።
ነገር ግን በዕቅዱ መሠረት እስራኤል ወታደሮቿን በማስውጣት ጋዛን ለሚሰማራው ኃይል ስታስረክብ ሐማስም ትጥቁን መፍታት ይጠበቅበታል። ትጥቅ የማስፈታቱ ሁኔታ በምን ያህል መጠን እና እንዴት ይከናወናል የሚለው ገና በውል ያልለየለት ጉዳይ መሆኑን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
የፕሬዝዳንቱን ዕቅድ ለማስፈጸም ዋነኛው ኃላፊነት ያለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዓለም አቀፉ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሰባስቦ ሥራውን የሚጀምርበት ሁኔታ እንደሚመቻች አመልክተዋል።
“በሁሉም ወገኖች ተቀባይነት ያላቸው በርካታ አገራት ፈቃደኛ በመሆን የአረጋጊው ኃይል አካል ለመሆን ፈቃደኛ እንደሚሆኑ በጣም እርግጠኛ ነኝ” ሲሉ ሩቢዮ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
ወደ ጋዛ ወታደሮችን ማሰማራት
በጋዛ የተካሄደውን የሁለት ዓመት ጦርነት ያስቆመው ስምምነት ሁለተኛው ምዕራፍ የሆነው የአረጋጊ ኃይል ስምሪት በአዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት መጀመሪያ ላይ እውን እንዲሆን የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጥረት እያደረጉ ነው።
ሮይተርስ የዜና ወኪል የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው በርካታ አገራት ለተልዕኮው አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎታቸውን መግለጻቸውን እና የኃይሉን መጠን፣ ተዋጽኦ፣ የሚሰፍርበትን ሁኔታ፣ ሥልጣን እና ኃላፊነቱን የሚወጣበት መመሪያ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ገልጿል።
እንዲሁም ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ ከ25 የሚበልጡ አገራት ተገኝተው ወደ ጋዛ የሚሰማራው ኃይል በሚኖረው የዕዝ ተዋረድ እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዕቅድ ለማውጣት ኳታር ዶሃ ውስጥ ስብሰባ አካሂደዋል።
በፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚመራው የጋዛ የሰላም ዕቅድ አካል የሆነው የመረጋጋት ኃይል በአሜሪካዊ ጄነራል እንዲመራ የታሰበ መሆኑ ተነግሯል።
ጋዛ ውስጥ የሚሰማሩ ወታደሮችን ማዋጣት ዋነኛው ጥያቄ ሲሆን፣ ነገር ግን የወታደሮች ስምሪትን ጨምሮ አምስት ዋነኛ አገራት የሚሳተፉቸባው መስኮች አሉ።
እነዚህም ወታደሮችን በማሰማራት፣ ሕግ አስከባሪ መኮንኖች፣ የገንዘብ እና የአቅርቦት ድጋፍ፣ ፍልስጤማውያን ፖሊስ መኮንኖችን ማሠልጠን እና መደገፍ ናቸው።
ዕቅዱን እየመራች ያለችው አሜሪካ ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ወደ 10 ሺህ የሚደርሱ ሕብረ ብሔራዊ ወታደሮችን በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት አሰባስባ ለማሰማራት ትሻለች። ነገር ግን ከስምንት ሺህ የሚልቁ ወታደሮችን ማግኘት አትችልም በማለት ጥርጣሬያቸውን ይገልጻሉ።
በጋዛ ውስጥ ለሚሰማራው ኃይል አስተዋጽኦ ለማበርከት ፍላጎታቸውን ካሳዩት 19 አገራት መካከል አብዛኞቹ በቁሳቁስ፣ በአቅርቦት እና በትራንስፖርት ዙሪያ ለመሳተፍ የወሰኑ ሲሆን፣ ወታደሮችን በመላኩ በኩል ግን በተጨባጭ የተባለ ነገር የለም።
ሳዑዲ አረቢያን እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትን ጨምሮ በርካታ የመካከለኛው ምሥራቅ መንግሥት እና የአሜሪካ ወዳጆች ለሚሰማራው ኃይል የሚያስፈልገውን ገንዘብ ለማሰባሰብ እየሠሩ መሆናቸው ተነግሯል።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወታደሮችን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት
አሜሪካ የተለያዩ የዓለም አገራት በጋዛ ሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥረት እደያረገች መሆኗን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።
አሜሪካ የምትፈልገውን ያህል ወታደሮች በጋዛ ለሚሰማራው ኃይል በጊዜው ማግኘት ባለመቻሏ በከፍተኛ ባሥልጣናቷ በኩል አገራት እንዲሳተፉ እያግባባች ነው።
አገራት ወታደሮቻቸውን እንዳያሳትፉ ምክንያት ከሆኗቸው ምክንያቶች መካከል የአረጋጊው ኃይል ሥልጣን እና ኃላፊነት እስከ ምን ድረስ እንደሚሆን ግልጽ አለመሆኑ ነው። ይህንንም ችግር ለመፍታት በዶሃው ስብሰባ ላይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ቀርቦ ነበር።
በተጨማሪም በጋዛ ውስጥ የሚሰማሩት ወታደሮች የሐማስ ተዋጊዎችን ትጥቅ እስከ ማስፈታት የሚደረስ ኃላፊነት በትራምፕ ዕቅድ ውስጥ በመካተቱ ይህም አገራት ወታደሮቻቸውን ጋዛ ውስጥ ከሐማስ ጋር ፍልሚያ ውስጥ እንዲገቡ ሊያደርግ ይችላል የሚል ስጋት በመፍጠሩ ነው።
በእርግጥም የትጥቅ መፍታት ጉዳይ በሐማስ በኩል ሙሉ ተቀባይነት የለውም። በቅርቡ የሐማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ኻሊድ ማሻል ለአል ጀዚራ “ሙሉ ትጥቅ መፍታትን የሚመለከተው ሃሳብ ከሐማስ በኩል ተቀባይነት የሌለው ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ነገር ግን እስራኤል እና አሜሪካ ፍልስጤማዊው ቡድን ትጥቁን እንዲፈታ ያለማቋረጥ ሲጠይቁ ቆይተዋል። የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የሐማስ ትጥቁን ማስረከብ “ቁልፍ ጉዳይ” ነው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተው ነበር።
አሜሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል ለማሰባሰብ እየተጣደፈች ባለበት ሁኔታ የሐማስ ትጥቅ መፍታት ጉዳይ ላይ አስቸኳይ ግልጽ ያለ ውሳኔ እና ስምምነት ላይ ካልተደረሰ የታሰበው የጋዛ አረጋጊ ኃይል ስምሪትን ከማደናቀፍ አልፎ ሌላ ዙር ግጭትን እንዳይቀሰቅስ ያሰጋል።
የፎቶው ባለመብት, Ali Jadallah/Anadolu via Getty Images
የትኞቹ አገራት ወታደሮች ሊያዋጡ ይችላሉ?
በርካታ አገራት በጋዛ ዓለም አቀፍ አረጋጊ ኃይል ውስጥ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ አስተዋጽኦ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹ ቢሆንም በተጨባጭ ምን ያህል ወታደሮችን ለማሰማራት ወይም የገንዘብ ድጋፍ እንደሚሰጡ ይፋ የሆነ ነገር የለም።
ከመነሻው አሜሪካ፣ ግብፅ፣ ዮርዳኖስ፣ የተበባሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኳታር የሰላም አስከባሪውን ስምሪት ተግባራዊ ለማድረግ ከፊት ሆነው እየጣሩ ነው። ነገር ግን ወታደሮቻቸውን ስለማሰማራታቸው ምንም ፍንጭ አልሰጡም።
ነገር ግን የሩቅ ምሥራቋ አገር ኢንዶኔዢያ በጤና እና በመልሶ ግንባታ ውስጥ የሚሳተፉ እስከ 20 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮችን ለማዋጣት ፈቃደኛ በመሆን ቀዳሚ ናት። በተመሳሳይ አውሮፓዊቷ ጣልያንም ለጋዛ ሰላም ወታደሮቿን እንደምትልክ የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ ዘግቧል።
ቱርክ ወታደሮቿን የማሳተፍ ፍላጎት እንዳላት ብትገልጽም በጋዛው ጦርነት ወቅት በነበራት አቋም ምክንያት እስራኤል ተሳትፎዋን አልተቀበለችውም። እንዲሁም የቱርክ ወዳጅ የሆነችው አዘርባጃን ከመነሻው ፈቃደኝነቷን ገልጻ የነበረ ቢሆንም ሃሳቧን ለመቀየር እያንገራገረች መሆኗን አንዳንድ ሪፖርቶች እየጠቆሙ ነው።
አሜሪካ የጋዛ አረጋጊ ኃይል በአጭር ጊዜ ተዋቅሮ ዋነኛ ጉዳይ የሆኑትን ወታደሮች ከተለያዩ አገራት በማሰባሰብ በትራምፕ የተኩስ አቁም ዕቅድ መሠረት በጋዛ ውስጥ ተሰማርተው ሁለተኛው ምዕራፍ ስምምነት ስኬታማ እንዲሆን እየጣረች ነው።
እስካሁን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት 70 አገራት በተለያየ መልኩ በጋዛ በሚሰማራው ኃይል ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥያቄ ማቅረቡን እና 19 አገራት ወታደሮችን ለመላክ ወይም የተለያየ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን እንዳሳወቁ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።
ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በዚህ ተልዕኮ ውስጥ እንዲሳተፉ ከተጠየቁት አገራት መካከል ከአፍሪካ የሦስት አገራት ስም ተጠቅሷል።
የጋዛ ተጎራባች እና የተኩስ አቁም እንዲደረስ ጉልህ ሚና የነበራት ግብጽ ዋነኛዋ ስትሆን፣ በምን መልኩ እንደምትሳተፍ ባይገለጽም ሞሮኮም ያለችበት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ወታደሮች እንድትልክ ተጠይቃለች ተብሏል።
የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለኢትዮጵያ ቀረበ የተባለው ጥያቄ
ከኢትዮጵያም ሆነ ከአሜሪካ መንግሥት በኩል አስካሁን ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ባይሰጥም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የጋዛ አረጋጊ ኃይል ውስጥ ወታደሮቿን እንድታሳትፍ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ መጠየቋ ተዘግቧል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሁለት ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ነገሩኝ ብሎ ‘ታይምስ ኦፍ ኢዝራኤል’ ባወጣው መረጃ ምንም ዓይነት ዝርዝር ሳይገለጽ ኢትዮጵያ ለጋዛ ሰላም አስከባሪ ኃይል ወታደሮችን እንድታዋጣ ከአሜሪካ ጥያቄ ቀርቦላታል ሲል ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጥቂት ሳምንት በፊት ኅዳር 24/2018 ዓ.ም. የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ “የአፍሪካ ቀንድ ሰላም” እና “ቀጣናዊ መረጋጋትን” በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በስልክ መነጋገራቸውን መሥሪያ ቤታቸው ማስታወቁ ይታወሳል።
ነገር ግን በአሜሪካው እና በኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል የተደረገውን የስልክ ውይይትን በተመለከተ ምንም ዓይነት ዝርዝር ካለመውጣቱ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ስለንግግሩ የተባለ ነገር የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ በኅዳር ወር ማብቂያ ላይ ያደረጉት ውይይት በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን፣ የቀደመው ነሐሴ አጋማሽ ላይ የተደረገ ነበር።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የስልክ ውይይት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ የአሜሪካ ጦር ሠራዊት የአፍሪካ ዕዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አንደርሰን በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሁም ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ተወያይተው ነበር።