ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በብራውን ዩኒቨርሲቲ በተፈጸመ የጅምላ ጥቃት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የአሜሪካን ግሪን ካርድ ሎተሪን (ዲቪ) አገግደዋል።
ጥቃቱን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረው እና ሐሙስ ዕለት ሞቶ የተገኘው ፖርቹጋላዊው እአአ በ2017 ዲቪ ሎተሪ አሸንፎ ወደ አሜሪካ የገባ ሲሆን ግሪን ካርድም ተሰጥቶታል።
ዳይቨርሲቲ ቪዛ ወይም ዲቪ ሎተሪ በአሜሪካ በስደተኝነት በቂ ድርሻን ላላገኙ አገራት ታስቦ የተዘጋጀ ሰሆን፤ በየዓመቱ 50 ሺህ ቪዛዎች የሚሰጡበት አሠራር ነው። ዲቪ የአሜሪካ ዜግነትን ለማግኘት ይረዳል።
የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር ክሪስቲ ኖም፤ ትራምፕ ዲቪ እንዲቋረጥ የወሰኑት “በዚህ አስከፊ [የዲቪ] ፕሮግራም ምክንያት አሜሪካውያን ከዚህ በኋላ እንዳይጎዱ” ነው ብለዋል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተጠርጣሪው የ48 ዓመቱ ክላውዲዮ ኔቭስ ቫለንቴ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም (ኤምአይቲ) ፕሮፌሰር ኑኖ ሉሬሮንም ገድሏል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
የዲቪ ታሪክ
ዲቪ በአሜሪካ ቋሚ መኖሪያ ፈቃድ (ግሪን ካርድ) ለማግኘት ቀላሉ መንገድ ነው።
እአአ በ1986 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬገን፤ አሜሪካ በሕገ ወጥ መንገድ ለሚኖሩ 2 ሚሊዮን ሜክሲኳውያን ቋሚ መኖሪያ ፈቃድ ሰጥተዋል።
በአሜሪካ የተለያዩ የዘር ሐረጎች ስብጥር አለመኖር ፕሬዝዳንቱን ያሳስባቸው ነበር። የአገሪቱን ነዋሪዎች ስብጥር ለማረጋገጥም ዲቪ ሎተሪ ተጠነሰሰ።
ለዲቪ ማመልከት ቀላል እንዲሆን የተደረገው ሁሉም ሰው የማመልከት ዕድል እንዲያገኝ ነው።
በ1987 ለመጀመሪያ ጊዜ ዲቪ ሲተዋወቅ ‘ኤንፒ-5 ሎተሪ ፕሮግራም’ የሚል ስም ተሰጠው። ለሁለት ዓመታት ያህል በየዓመቱ ከ36 አገራት ለተውጣጡ 5000 ሰዎች ቪዛ ተሰጠ።
ከሁለት ዓመታት በኋለ የቪዛው ቁጥር 15,000 ደረሰ።
ከ1990 እስከ 1991 ‘ኦፒ-1 ፕሮግራም’ በሚል ስም ይታወቅ ነበር። 10,000 ቪዛዎችም ተሰጥተዋል።
በቀጣይ ሁለት ዓመታት ስሙ ‘ኤኤ-1 ፕሮግራም’ ተብሎ ከ37 አገራት ለተውጣጡ 40,000 ሰዎች ቪዛ ተሰጠ። 16, 000 ቪዛዎች የተመደቡት ለሰሜን አየርላንድ ነበር።
እአአ በ1994 ዲቪ አሁን ያለውን ቅርጽ እንዲይዝ ተወሰነ። ስደተኞች በብዛት ከሚገኙባቸው አገራት ውጭ ላሉ 55,000 ቪዛዎች ተመደቡ።
ባለፉት አምስት ዓመታት ከ50,000 በላይ ሰዎች በቪዛ አሜሪካ ገብተዋል።
በ2003 ቪዛ በበይረ መረብ የማመልከት አሠራር ተዘረጋ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የዲቪ ማመልከቻ በወረቀት ተጽፎ ይላክ ነበር።
በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዲቪ ጥያዌዎችን አሜሪካ ይደርሷታል።
ለዲቪ በየዓመቱ 50,000 ቪዛ ይመደባል። በዚህ ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ አገራት በየዓመቱ ይለዋወጣሉ። ይህም በአሜሪካ የዜግነት እና ስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት ድረ ገጽ ላይ ይገኛል።
በ2025 ወደ 20 ሚሊዮን ሰዎች ዲቪ ሞልተዋል።
የዲቪ ዕድል እንዲገደብ የሚደረግባቸው አገራት ባለፉት አምስት ዓመታት ከ50,000 በላይ ስደተኞችን ወደ አሜሪካ የላኩ ናቸው። ወደ አሜሪካ የገቡት ሰዎች በቤተሰብ ወይም በሥራ ሊሆን ይችላል ዕድሉን ያገኙት።
ለ2026 የሥራ ዘመን 55,000 ቪዛዎች ቢመደቡም የዲቪ ጉዳይ በትራምፕ ውሳኔ ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ወድቋል።
ዲቪ ማሸነፍ ወዲያውኑ የአሜሪካ ዜጋ አያደርግም። የተመረጡት ሰዎች ለዜግነት ማመልከት አለባቸው። የአሜሪካ መንግሥት ያስቀመጠውን መስፈርት ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ዲቪን የሚደለድለው በስድስት የዓለም ክፍሎች ሲሆን፤ በኮምፒውተር የታገዘ ዕድልን መሠረት ያደረገ እጣ አወጣጥ ነው።
ለሁሉም አገራት በየዓመቱ ሰባት በመቶ የዲቪ ሎተሪ ዕድል ይሰጣል።
በ2025፤ ከ131,000 በላይ ሰዎች ዲቪ አግኝተዋል። በብራውን ዩኒቨርስቲ ጥቃት የፈጸመው ፖርቹጋላዊ ሲሆን ለፖርቹጋል የተመደበው 38 ዲቪ ነው።
የአገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስትር የሆኑት ክሪስቲ ኖም፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፕሮግራሙን ለማስቆም “ታግለዋል” ብለዋል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ትራምፕ ቀደም ሲል በኒው ዮርክ ከተማ ስምንት ሰዎች በጭነት መኪና ተገጭተው ከተገደሉ በኋላ ፕሮግራሙን ለማስቆም “ታግለዋል” ብለዋል።
ኖም እንዳሉት የኡዝቤኪስታን ተወላጅ የሆነው ሳይፉሎ ሳይፖቭ፣ የኢስላሚክ ስቴት ደጋፊ የሆነ እና ለተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ግለሰብ በዲቪ1 ፕሮግራም መሠረት ወደ አሜሪካ ገብቷል።
የብራውን ዩኒቨርስቲ ጥቃት ፈጻሚ ነው የተባለው ኔቭስ ቫለንቴ በሳሌም፣ ኒው ሃምፕሻየር በሚገኝ መጋዘን ውስጥ ሞቶ ተገኝቷል።
ግለሰቡ ሕይወቱ ያለፈው ራሱ ተኩሶ ሊሆን አንደሚችል ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ከሕዝብ የተላኩ የቪዲዮ ማስረጃዎችን እና ጥቆማዎችን በመጠቀም መርማሪዎቹን ወደ መኪና ማከራያ ከላከ በኋላ የተጠርጣሪውን ስም ማግኘት መቻሉን ይፋ አድርጓል።
ለስድስት ቀን ያህል ግለሰቡን ሲፈልግ የነበረው ፖሊስ በስተመጨረሻም ተጠርጣሪውን አግኝቷል። አንድ ሻንጣ እና ሁለት የጦር መሣሪያዎች ከተጠርጣሪው አስከሬን ጎን ተገኝቷል።
በአቅራቢያው ባለ መኪና ውስጥ የተገኙ ቁሰቁሶች ከብራውን ዩኒቨርሲቲ ከተሰበሰቡ ማስረጃዎች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን የሮድ አይላንድ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ፒተር ኔሮንሃ ተናግረዋል።
የብራውን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ክርስቲና ፓክስሰን እንዳሉት፤ ኔቭስ ቫለንቴ ስመ ጥር በሆነው ትምህርት ቤት ተመዝግቦ በፊዚክስ የዶክትሬት ዲግሪውን ለማግኘት እየተማረ ነበር።
ባለሥልጣናት እንዳሉት ኔቭስ ቫለንቴ ሰኞ ዕለት የ47 ዓመቱን የኤምአይቲ ፕሮፌሰር ኑኖ ኤፍ ጎሜስ ሉሬሮ ከፕሮቪደንስ፤ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ብሩክሊን በሚገኘው ቤታቸው ተኩሶ ገድሏል ብለው ያምናሉ።
ሁለቱም ሰዎች በ1990ዎቹ መጨረሻ ላይ በፖርቹጋል በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተምረው እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።
ባለሥልጣናት፤ የተጠርጣሪው ተሽከርካሪ በደኅንነት ካሜራ መታየቱን እና በብራውን ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ አንድ የዐይን ምስክር ከሰጡት ቃል በመነሳት ተጠርጣሪው ወንጀሉን መፈጸሙን ማመናቸውን ተናግረዋል።
ይሄው መኪና ፕሮፌሰሩ በጥይት በተገደሉበት ቦታ አቅራቢያ ታይቶ ነበር። ባለሥልጣናት ለጥቃቱ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ይፋ አላደረጉም።
በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 13/2025 አንድ ታጣቂ በብራውን ዩኒቨርሲቲ የምህንድስና ትምህርት ክፍል ሕንጻ ውስጥ በመግባት ተኩስ ከፍቶ ሁለት ተማሪዎች ሲሞቱ ሌሎች ዘጠኝ ደግሞ ቆስለዋል።
የትራምፕ እርምጃ
አሜሪካ ከአውሮፓውያን አቆጣጠር 1995 ጀምሮ በዲቪ ሎተሪ አማካኝነት ወደ አገሯ በርካቶች እንዲገቡ ብትፈቅድም የዲቪ 2027 ማመልከቻ ጊዜ ዘግይቶ ነበር።
የዘንድሮ አመልካቾች 1 ዶላር እንዲከፍሉ ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ከተለመደው የማመልከቻ ጊዜ ስለዘገየበትም ሆነ ስለክፍያው በይፋ የተነገረ ነገር የለም።
ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ የተለያየ እርምጃ ወስደዋል።
በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሰነድ አልባ ስደተኞችንም ወደመጡበት ለመመለስ እየሠሩ ነው።
አንድ የአፍጋኒስታን ስደተኛ በዋሽንግተን ዲሲ ሁለት የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ አባላትን በጥይት ተኩሶ አንዷን ከገደለ እና ሌላኛውን ካቆሰለ በኋላ የትራምፕ አስተዳደር ከ19 አገሮች የመጡ ስደተኞች የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ላይ ዳግም ፍተሻ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ አፍጋኒስታናውያንን ጨምሮ የበርካታ አገራት ስደተኞችን የጥገኝነት ጥያቄ ሂደት በማቆም ተከታታይ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።
ትራምፕ ዲቪን ማገዳቸው ኢትዮጵያውያን ላይ ምን ጫና ያሳድራል?
ወደ አሜሪካ ጥቂት ስደተኞች የሚልኩ አገሮች በዋነኛነት በዲቪ ሎተሪ መቋረጥ ተጎጂ ይሆናሉ።
በቅርብ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት እገዳው በዋነኛነት ጫና የሚያሳድረው በኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና የአረብ አገራት ነው።
ከዚህ ቀደም እገዳ ከተጣለባቸው አገራት መካከል ባንግላዲሽ፣ ብራዚል፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ፊሊፒንስ፣ ደቡብ ኮርያእና ቬትናም ይገኙበታል።
በቤተሰብ እና በሥራ ዜጎቻቸውን ወደ አሜሪካ የሚልኩት እነዚህ አገራት በዲቪ መታገድ የበለጠ ጫና ውስጥ ይወድቃሉ።
ትራምፕ የጉዞ እገዳ የጣሉባቸው የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ባለፉት ሳምንታት በተጣለባቸው የጉዞ እገዳ ላይ የዲቪ ሎተሪ መቋረጥ ይደራረብባቸዋል።
በዋነኛነት የሚጎዱ አገራት ዝርዝር-
- አፍሪካ- ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ሞሮኮ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ቱኒዝያ
- እስያ- ባንግላዲሽ፣ ቻይና (ሆንግ ኮንግን ጨምሮ)፣ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ፊሊፒንስ፣ ደቡብ ኮርያ እና ቬትናም
- ላቲን አሜሪካ- ብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ዶምኒካን ሪፐብሊን፣ ኤል ሳልቫዶር፣ ሔይቲ፣ ሆንዱራስ፣ ሜክሲኮ እና ቬንዝዌላ
አንዳንድ የአፍሪካ እና አረብ አገራት ከደኅንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በትራምፕ እገዳ ተጥሎባቸዋል።
ትራምፕ እግዶችን ሲጥሉ የቆዩት በዋነኛነት የደኅንነት ስጋትን በማጣቀስ ነው።
በዲቪ መቋረጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በየዓመቱ ዲቪ የሚሞክሩ ሰዎችን አጣብቂኝ ውስጥ ይከታል። ዲቪ ደርሷቸው ለቪዛ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ የሚጠብቁ ሰዎችንም እንደዚሁ።
በዲቪ ወደ አሜሪካ ለመግባት እየሞከሩ ያሉ ቤተሰቦች ጉዳይም በእንጥልጥል ላይ ይገኛል።
የትራምፕ ውሳኔ አፍሪካን፣ እስያን እና ላቲን አሜሪካን በግንባር ቀደምነት ይጎዳል።
ትራምፕ ዲቪን ለማስቆም መዛት ከመጀሩ ቆይተዋል።
በተለይም በኒው ዮርክ ከተማ ስምንት ሰዎች በጭነት መኪና ተገጭተው ከተገደሉ በኋላ ፕሮግራሙን ለማስቆም ሞክረዋል።
በጥቃቱ የተጠረጠረው የኡዝቤኪስታን ተወላጅ የሆነው ሳይፉሎ ሳይፖቭ ሲሆን፤ የኢስላሚክ ስቴት ደጋፊ እንደሆነ ተገልጿል። ለጥቃቶች በርካታ የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ይህ ግለሰብ በዲቪ1 ፕሮግራም ነበር ወደ አሜሪካ የገባው
ሪፐብሊካኖች ያቀረቡት አንደኛው ሐሳብ ቤተሰቦችን የሚያካትት የመኖሪያ ፈቃድ አሠራርን ማጠፍ ነው። ትራምፕም ይሄንን ሐሳብ ይደግፋሉ።
ቤተሰቦችን የሚያቅፈው አሠራር ታጥፎ ሙያተኞችን በብቃታቸው በመመዘን የሚቀበል የቪዛ አሠራር ትኩረት እንዲሰጠው ትራምፕ ይፈልጋሉ።
እነዚህ ስደተኞች ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸው እና ጥሩ እንግሊዘኛ ተናጋሪ እንደሆኑ ይፈለጋል።
የአሜሪካ ፌደራል መንግሥት መረጃ እንደሚጠቁመው በ2026 ለዲቪ ካመለከቱ ሰዎች አብላጫውን ቁጥር የያዙት ከአፍሪካ፣ እስያ እና አውሮፓ ናቸው።
ዲቪ የሚያመለክቱ ሰዎች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል። ወይም ደግሞ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተጨባጭ የሥራ ልምድ ማሳየት አለባቸው።
ዲቪ ለዕድለኞች የሚሰጥ ቢሆንም አሜሪካ የደኅንነት ፍተሻ ታደርጋለች። በአንዳንድ ሁኔታዎች አሜሪካ ውስጥ ያሉ ሰዎችም ዲቪ ሊያመለክቱ ይችላሉ።
አሜሪካ ውስጥ በተለያየ የስደተኞች ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ሰዎች ቋሚ መኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት ዲቪ ያመለክታሉ።
ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በጉዞ እገዳቸው ውስጥ ተጨማሪ አገራት እንዲካተቱ ወስነዋል።
አጠቃላይ እገዳ ከተጣለባቸው መካከል ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶሪያ እና ፍልስጤም ይገኙበታል።
ከፊል እገዳ ዝርዝር ውስጥ የነበሩት ላኦስ እና ሴራ ሊዮን አጠቃላይ እገዳ ውስጥ ተካተዋል። ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ እና ዚምባብዌን ጨምሮ ሌሎች አገራት ከፊል እገዳ ተጥሎባቸዋል።
በድጋሚ ሥልጣን የያዙት ትራምፕ ስደተኞች ላይ ጥብቅ እርምጃ መውሰዳቸውን ቀጥለዋል።
ከተለያዩ አገራት ወደ አሜሪካ የሚገቡ ስደተኞች ላይ የሚደረገው ፍተሻ ጠንካራ አይደለም በሚል ትራምፕ ተችተዋል።