የፎቶው ባለመብት, presidency.eg
ግብፅ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጋር ሕጋዊ አስገዳጅ ስምምነት ላይ ከመድረስ በስተቀር ሌላ ምንም ዓይነት “ችግር እንደሌለባት” ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አልሲሲ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት ግብፅ ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘው ሁለተኛው የሩሲያ እና የአፍሪካ የትብብር መድረክ የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ካይሮ ከሚገኙ የአፍሪካ አገራት ልዑካን ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ መሆኑን መንግሥታዊው አል አህራም ዘግቧል።
ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር “ችግር የለባትም” ያሉት አል ሲሲ ነገር ግን “ብቸኛው ፍላጎቷ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት መብት እንዳይነካ ማድረግ ነው፤ ለዚህም ሕጋዊ እና አስገዳጅ ስምምነት እንዲደረስ ነው” በማለት ኢትዮጵያ ገንብታ ሥራ ባስጀመረችው የሕዳሴ ግድብ ላይ የአገራቸውን አቋም በጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል ተብሏል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ ለ13 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር የተደረጉ ንግግሮች ውጤት ያስገኙ ባለመሆናቸው አገራቸው ተጨማሪ ውይይት እንደማትፈልግ እና መብቷን በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት እንደምታስከብር ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የግድቡ ግንባታ በተካሄደበት አስራ አራት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ እና በግብፅ እንዲሁም በሱዳን መካከል በተደጋጋሚ ሲቋረጥ እና ሲቀጥል የቆየ ድርድር በተለያዩ አገራት እና ተቋማት አሸማጋይነት ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።
በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ አሁን ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ያነሱት የግድቡን ውሃ አሞላል እና ዘላቂ አስተዳደርን በተመለከተ ሕጋዊ እና አስገዳጅ ስምምነት ኢትዮጵያ እንድትፈርም በተደጋጋሚ ከግብፅ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከስምምነት ላይ ላለመድረሳቸው ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።
ግብፅ የምትጠይቀው ታሪካዊ የአባይ ውሃ ድርሻዋንም በተመለከተ ኢትዮጵያ ባልተካተተችበት እና ምንም ድርሻ ባልነበራት ኢ-ፍትሐዊ ባለችው የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነት እንደማትገዛ በመግለጽ ውድቅ አድርጋለዋች።
የአባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ ውሃውን የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ሲሆን፣ የወንዙን አብዛኛውን ውሃ የምትጠቀመው ግብፅ በኢትዮጵያ የተገነባው ግድብ ብቸኛ የውሃ ምንጭ መጠን ያሳጣኛል የሚል ስጋት ፈጥሮባታል።
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመው እና አብዛኛውን የወንዙን ውሃ ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት በመጥቀስ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት አላት በማለት ኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳላበት ስትከራከር ቆይታለች።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የግብፅን የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ የሚጥል አይደለም ስትል በተደጋጋሚ ገልጻለች።
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ከአፍሪካ አገራት ተወካዮች ጋር ቅዳሜ ዕለት ባደረጉት ውይይት ላይ ግብፅ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ አለመግባት እና አለመረጋጋትን በማስወገድ በኩል ያላት ፖሊሲ ወጥ እና ጽኑ ነው ማለታቸውን ከጽሕፈት ቤታቸው የወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው ጠንካራ መግለጫ ግብፅ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ ጥረት እያደረገች ነው በማለት ከስሷል። የዚህም ዋነኛ ትኩረት ኢትዮጵያ እንደሆነች እና አጠቃላይ ቀጣናውንም የማናጋት ፍላጎት አለ ብሏል።
በተጨማሪም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኢትዮጵያ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን በሚቀርቡ ዘገባዎች እና ውይይቶች ላይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ትጥቅና ድጋፍን ከግብፅ እንደሚያገኙ የሚገልጹ ክሶች በተደጋጋሚ ይደመጣሉ።
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ በተጨማሪም አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ልዩነት ቢኖራትም አለመግባባቶች በውይይት እና በፖለቲካዊ መፍትሄ በፈታት አለባቸው በሚል አቋም “ግብፅ ማስፈራሪያዎችን ሰንዝራ አታውቅም” ሲሉ ተናግረዋል።
ነገር ግን ፕሬዝዳንቱ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና ሌሎች የግብፅ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ የአገራቸውን ጥቅም እና የውሃ ደኅንነት ለማስከበር አስፈላጊውን ሁሉ እርምጃ እንደሚወስዱ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል።
እነዚህን የግብፅ ባለሥልጣና ንግግርን ተከትሎም የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ ግብፅ ከንግግር ይልቅ “ግጭትን ለማስፋፋት ግልጽ ፀብ አጫሪ ንግግሯን እያጠናከረች ነው” በማለት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን ድርጊት እንዲያወግዝ ጠይቋል።
ግብፅ የውሃ ደኅንነቴ እና ብሔራዊ ጥቅሜ ላይ አደጋን ደቅኗል ባለችው የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ ፍላጎቷን የሚስጠብቅ ሕጋዊ እና ኢትዮጵያን ግዴታ ውስጥ የሚስገባ እንዲሆን ትፈልጋለች።
ኢትዮጵያ ግን እንዲህ ያለው ስምምነት ሉዓላዊነቷን እና ጥቅሟን አሳልፎ የሚሰጥ መሆኑን በመጥቀስ በተደጋጋሚ ውድቅ ስታደርገው ቆይታለች።
ፕሬዝዳንት አል ሲሲ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይን ከዚህ ቀደም ወደ አፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ አረብ ሊግ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ እና ሌሎች አገራት ዘንድ በመውሰድ በኢትዮጵያ ላይ ግፊት ለማሳደር ሲሞክሩ ቆይተዋል።