“በጋምቤላ ክልል ያሉ ስደተኞችን በተመለከተ የሚሰራጨው ሐሰተኛ መረጃ አሳስቦኛል” የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ

“በጋምቤላ ክልል ያሉ ስደተኞችን በተመለከተ የሚሰራጨው ሐሰተኛ መረጃ አሳስቦኛል” የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ

የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ስደተኞችን ኢላማ ያደረጉ የተሳሳቱ መረጃዎች መሰራጨታቸው እንዳሳሰበው ገልጿል።

ኤጀንሲው ስደተኞቹ በሃገራቸው ካጋጠማቸው ግጭት የተነሳ ደኅንነትና ጥበቃ ፈልገው መጥተዋል ያለ ሲሆን ሁሉም ሰው ስደተኞች እና ስደተኞቹን የተቀበሉ ማኅበረሰቦች ላይ የጥላቻ ንግግርን እንዳይደረግ ጠይቋል።

የተመድ ኤጀንሲ በክልሉ የተከሰተው ሁኔታ የምግብ እና ውሃ ሥርጭትን ጨምሮ አንዳንድ አገልግሎቶች በጊዜያዊነት እንዲቆሙ ማስገደዱን አንስቶ ሁኔታውን እየተከታተለ ስለመሆኑና ከአስተዳደር አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

እንደ የስደተኞች ኤጀንሲው ዘገባ ከ482 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያ የሚገኙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ447 ሺህ በላዩ የሚገኙት በጋምቤላ ክልል ነው።

ከባለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ ደግሞ ከ50,000 በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ወደ ጋምቤላ ክልል መግባታቸውም ተገልጿል።