” ቤቴና መሶቤ ሙሉ ነበር ከቀዬ ከተፈናቀለኩ በኃላ ግን ሁሉ ባዶ ታሪክ ሆኗል ፤ እኔና 6 ቤተሰቦቼ ከምንበላው ጦማችን የምናድርበት ጊዜ ይበዛል ድረሱልን ” – በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃይ
➡️ ” ጊዚያዊ አስተዳደሩና የመንግስት መዋቅሩ ረሀቡ መከሰቱ በማህበራዊ የትስስር ገፃች ከመነገሩ በኃላ መንቃቱ የአመራር ክፍተት ዋነኛ ማሳያ ነው ” – አስተያየየት ሰጪዎች
በትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አስገደ ወረዳ ከእንዳስላሰ-ሽረ ከተማ አቅራቢያ የምትገኘው #ሕፃፅ ከደም አፈሳሹ የትግራይ ጦርነት በፊት የኤርትራ ስደተኞች ማቆያ በመሆን ትታወቃለች።
በሕፃፅ የስደተኞችና የተፈናቃዮች የመጠለያ ጣብያ የዛሬውን ያህል በእህል፤ ውሃና ህክምና እጦት የገረጡ ፊቶች ታይተው አያውቁም።
ሕፃፅ በዙሪያዋ ከሚገኘው የወርቅ ማዕድን ሀብት በሚሊዮን የሚገመት ብር የሚዛቅበት ሆና ሳለ በጉያዋ ግን በሀይለኛ ረሀብና ውሃ ጥም ተፈናቃዮች ወደ መቃብር ይሸኙባታል።
አርሶ አደር ጉዕሽ በትግራዩ ጦርነት ምክንያት ከምዕራባዊ ዞን አደባይ ከተባለ ሰፊ እርሻ ያለበት ቦታ ተፈናቅለው በሕፃፅ የመጠለያ ጣብያ በአሮጌ ፕላስቲክ በተሰራ ቤት መኖር ከጀመሩ 5 ዓመታት ተቆጥረዋል።
አርሶ አደሩ በመጠለያ ጣብያዋ ከሚገኙ 16 ሺህ ተፈናቃዮች መካከል ሲሆኑ ‘ አስቸኳይ እርዳታ ካላገኙ ለቀናት እንኳን በህይወት መቆየት ይከብዳቸዋል ‘ ተብለው በዞኑ ከተጠኑ 1,700 በላይ የተቸገሩ ወገኖች አንዱ ናቸው።
በድስት ያረረ ወጥ እያሳዩ ” ቤቴና መሶቤ ሙሉ ነበር ከቀዬ ከተፈናቀለኩ በኃላ ግን ሁሉ ባዶ ታሪክ ሆኗል ፤ እኔና 6 ቤተሰቦቼ ከምንበላው እራት ጦማችን የምናድርበት ጊዜ ይበዛል ድረሱልን ” ሲሉ ተማፅነዋል።
ሌላኛዋ ራሷና ሁለት ታማሚ ልጆችዋ ጊዜ በማይሰጠው ረሀብ ስር መሆናቸውን የገለጸች ተፈናቃይ ” በረሃብ ወለድ ሞት ምክንያት ሁለት ሰዎች እየቀብርን ነው ” በማለት ከቀናት በፊት ሞተው የተቀበሩ የአንድ አባት መቃብር አሳይታለች።
” ለረሃብ በሽታና ሞት የዳረገን ከቄያችን መፈናቀላችን ፤ መሬታችን ለማረስ አለመቻላችን ነው። ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን የሚፈቱት ወደ ቄያችን ስንመለሰ ብቻ ነው ” ብላለች።
በመጠለያ ማእከሉ የሚገኙ ተፈናቃዮች በወር 15 ኪሎ ስንዴ ነው የሚሰጣቸው፤ የብር 300 ዋጋ ያላት ስንዴ ለማስፈጨት ደግሞ 105 ብር ይጠየቃሉ።
” አመራሮች የህዝብን ጉዳይ ዘንግተውታል ” – አስተያየት ሰጪዎች
የምዕራብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ግደይ አዘናው እና መሰል የመንግስት አመራሮች በህዝቡ ክፉኛ ይተቻሉ።
” አመራሮቹ የህዝብ ጉዳይ ዘንግተው አብዛኛው ጊዚያቸው በፓለቲካ ሽኩቻ ባያውሉ ኖሮ በመጠለያ ጣብያው የተከሰተው አሰቃቂ ረሀብ ለመግታት ከአቅም በላይ አይሆንም ነበር ” ይላሉ ቃላቸውን የሰጡ አስተያየት ሰጪዎች።
” አመራሮቹ ህዝቡን መቅደም ሲገባቸው : ረሀቡ መከሰቱ በማህበራዊ የትስስር ሚድያዎች መቀጣጠሉ ተከትሎ መሯሯጣቸው ከህዝብ ዋነኛ አጀንዳ በምን ያህል እንደራቁ ዋነኛ ማሳያ ነው ” ሲሉ ተችተዋል።
በሕፃፅ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ከ2015 ዓ.ም ወዲህ 300 ሰዎች በረሃብና ረሀብ ወለድ በሽታ ለህልፈት መዳረጋቸው የሚገልፀው የዞኑ መረጃ 50ዎቹ በያዝነው ዓመት መሞታቸውን አረጋግጧል።
በመንግስት እውቅና ያለተሰጣቸው ሌሎች የመረጃ ምንጮች ደግሞ በመጠለያ ጣብያው ” በረሀብና ረሃብ ወለድ በሽታ ብቻ 350 ሰዎች አልቀዋል ” በማለት ይገልጻሉ።
እጅግ የዘገየም ቢሆን የክልሉ ጊዚያዊ አስተዳደር ካቢኔ ” በሕፃፅ የመጠለያ ጣብያ የተከሰተው አሰቃቂ ረሀብ በዘላቂ ለመግታት ” በሚል ዛሬ ሰኞ ታህሳስ 13/2018 ዓ.ም እየመከረ ይገኛል።
ምስጋና በትግራይ ለሚገኙ ወጣቶች ይሁንና በነሱ ምክንያት ችግሩ ወደ ማኅበራዊ ሚዲያው በመውጣቱ በአሁኑ ሰዓት ሕፃፅ የብዙዎች ትኩረት አግኝቷል። የምግብና የቁሳቁስ እርዳታ ከአቅጣጫው እየተሰበሰበ ነው።
ሰብአዊነት ከሚሰማቸው ለጋሽ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚሰጠው ድጋፍ በትክክል ረሀብ እየገረፋቸው ወደ ሚገኙች ተፈናቃይ ወገኖች መድረሱ ማረጋገጥ ግን ቀጣይና ዋና ስራ ነው።