” ልጆቼን እንዳይገደሉብኝ ጠብቅልኝ እያልኩ አምላኬን እየለመንኩ ነው ያለሁት ” – ልጆቻቸው የታገቱባቸው የ90 አመት አረጋዊ

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሮቤ ወረዳ  አምስት የአንድ ቤተሰብ አባላት በታጣቂዎች ታግተው መሰዳቸውን፣ ሁለቱ ቢመለሱም ሦስቱ ባለመለቀቃቸው የአካባቢው አመራሮች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ነዋሪዎችና ቤተሰቦቻቸው ጠየቁ።

እገታው የተፈጸመው ከአርሲ ሮቤ 6 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ “አኪያ” በሚባል ቦታ መሆኑን ገልጸው፣ “አምስት የአንድ ቤተሰብ ወንዶች አዝመራ በውቂያ ሳሉ በአካባቢው ባሉ የሸኔ ታጣቂዎች ተወስደዋል” ሲሉ ነዋሪዎቹ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

የታጋቾች አባትና አያት የሆኑ የ90 አመት የእድሜ ባለጸጋ ደግሞ፣ ሦስት ልጆቻቸው እና ሁለት የልጅ ልጆቻቸውን  በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

” ይህን ሊያሰማኝ አቆየኝ ” በማለት ሳግ የሚተናነቃቸው እኚሁ የእድሜ ባለጸጋ በገለጹት መሰረት፣ ልጆችና የልጅ ልጆቻቸው እህል ለመውቃት ነዶ ወደአውድማ እያስገቡ ባለበት ነው ” ከጫካ በወጡ የሸኔ ታጣቂዎች ” ታግተው የተወሰዱት።

እኝሁ አባት፣ ” ሐሙስ ታህሳስ 9 ቀን 2018 ዓ/ም ጠዋት 2 ሰዓት ተኩል ነው የእህል ነዶ እያጋዙ ባለበት የተወሰዱት። ነዶውን አውድማ አስገብተው ሊወቁ ነበር ” ነው ያሉት።

ምን ያክል ሰዎች እንደተወሰዱ ሲያስረዱም፣ “መጀመሪያ የተወሰዱት አምስት ናቸው፤ መጀመሪያ የተወሰዱት ሁለቱ የልጅ ልጆቼ ነበሩ ለቀቋቸው። ሦስቱን እንደወሰዷቸው ቀሩ ሦስቱ ልጆቼ ናቸው። ወደ ቄርቄር ውስጥ ከረዩ ስር ነው የወሰዷቸው” ብለዋል።

“አቆሙንና ‘የማናችሁ? አሉን’፣ ‘የአምዴ ነን አልናቸው’፤ ‘በሉ እናንተ ተመለሱ አሉን'” ሲሉ ከእገታ ተመላሾች መግለጻቸውን አስረድተው፣ “የተለቀቁት አባት አብሮ የታገተ ነው፤ የወሰዷቸው ከጫካ የወጡ ባለትጥቅ ናቸው” ብለዋል።

“እዚህ ነው ያሉት እንኳ አልተባልንም፤ ዝም ብለን ቁጭ ብለናል፤ ልጆቼን እንዳይገደሉብኝ ጠብቅልኝ እያልኩ አምላኬን እየለመንኩ ነው ያለሁት። አቅም የለኝም ከቤት የዋልኩ የ90 አመት ሽማግሌ ነኝ” ሲሉ አዝነዋል።