በሁለት ቀናት እስከ 20 ሰዎች ተገድለዋል፣ በአንድ ወረዳ ብቻ። በሌሎችም አሉ። ከሁለት ቀናት በፊትም በአቦል ወረዳ ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቁ በርካቶች ሞተዋል ” – የጋምቤላ ነዋሪዎች

” በሁለት ቀናት እስከ 20 ሰዎች ተገድለዋል፣ በአንድ ወረዳ ብቻ። በሌሎችም አሉ። ከሁለት ቀናት በፊትም በአቦል ወረዳ ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቁ በርካቶች ሞተዋል ” – የጋምቤላ ነዋሪዎች

➡️ ” በርካታ ቁስለኞች ወደ ህክምና ይላካሉ። በኛ ሆስፒታሉ የመጡት ብቻ ወደ 8 ይደርሳሉ። ጉዳት የደረሰባቸው ሦስት ሰዎች ወደ ጅማ ሪፈር ተደርገዋል” – በክልሉ በሚገኝ ሆስፒታል የሚሰሩ ሀኪም

በጋምቤላ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች በተለይ ከህዳር 30 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የበርካታ ንጹሐን ህይወት እየተቀጠፈ መሆኑን የሟች ቤተሰብ፣ ነዋሪዎችና በሆስፒታል የሚሰሩ ሀኪም ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።

አንዳንዶቹ የሟቾችንና ቁስለኞችን ቁጥር “ከ50 እስከ 60” ያደረሱት ሲሆን፣ ሌሎቹ ደግሞ “ከዚያም የበለጠ ነው” ይላሉ። ከቀናት በፊት ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ቃላቸውን የሰጡ አንድ የክልሉ ባለስልጣን “የሟቾች ቁጥር ከ10 በላይ ሊሆን ይችላል” ብለው ነበር።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ማበር ኮር ደግሞ፣ ሰዎች መሞታቸውን አምነው፣ ብዛታቸው ግን “10 እንደማይሆን” ሰሞኑን ነግረውን የነበረ ሲሆን፣ ነዋሪዎችና ጤና ባለሙያዎች ዛሬ እንደነገሩን ከሆነ ደግሞ ጥቃቱ ባለመቆሙ የሟቾና ተጎጅዎች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ ነው።

በሆስፒታል የሚሰሩ ሀኪምና ነዋሪዎች ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ምን አሉ ?

ነዋሪዎቹ በሰጡን ቃል፣ “በሁለት ቀናት እስከ 20 ሰዎች ተገድለዋል በአንድ ወረዳ ብቻ። በሌሎችም አሉ። ከሁለት ቀናት በፊትም በአቦል ወረዳ ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቁ በርካቶች ሞተዋል” ብለዋል።

የ27 አመት ወጣት በጸጥታው ችግር የተገደለባቸው ነዋሪ፣ “በጥይት ተመትቶ ነው  ያረፈው። ብዙ መንገዶች ዝግ ስለሆኑ በጥይት የተመቱ ሰዎች ህክምና ሳያገኙ እየሞቱ ነው። ወደ ህክምና ለመሄድ ጭምር መንገድ ዝግ ናቸው” ሲሉ በሀዘን ስሜት ገልጸዋል።

ሌሎች ነዋሪዎችም፣ በርካቶች ሙትና ቁስለኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ “የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ገብተው ጥቃት እያደረሱ ነው” የሚሉ መረጃዎች እየሰሙ መሆኑንም ተናግረዋል። የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ደግሞ “ውሸት ነው” ሲል ሰሞኑን መግለጹ ይታወሳል። ሌላኛው ለቲክቫህ ኢትየጵያ ቃላቸውን የሰጡ ነዋሪ ደግሞ፣ “እርስ በእርሳችን ነው የተጋጨነው እውነቱን ለመናገር” ይላሉ።

“ግን ‘የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ገብተዋል የሚሉም’ አሉ። አሁንም ሰው እየሞተ ነው። መንገድ ዝግ ነው። ቁስለኞች ህክምና የሚገኙበት ሁኔታ የለም። እንዲያውም ትናንት የቀበርነው ሰው የተመታው እግሩ ላይ ነበር ህክምና ስላላገኘ በመሀል ሞተ” ሲሉም ይናገራሉ።

የጸጥታ ችግር ባለባቸው ቦታዎች ያሉ ነዋሪዎች የሰሞንኛው ግጭት መነሻ ሲያስረዱ፣ ከላሬ ወረዳ የተነሰኑ ሁለት ተሽከርካሪዎች አቦል ወረዳ አካባቢ ሲደረሱ በተከፈተ የተኩስ ጥቃት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን፣ በዚሁ መነሻ ተኩሱ ተስፋፍቶ ህጻናት ጭምር እንደተገደሉ፣ አቦል ወረዳ ላይም የእርስ በእርስ ግጭት እንደተከፈተ አስረድተዋል።

በክልሉ በሚገኝ ሆስፒታል የሚሰሩ ሃኪም በሰጡን ቃል ደግሞ፣ “ከጸጥታው ሁኔታ ጋር በተያያዘ የተጎዱ ሰዎች ወደኛ እየተላኩ ነው” ብለዋል።

በተለይ ከባድ ጉዳት ለደረሰባቸው ቁስለኞች ህክምና ለመስጠት ከመንገድ መዘጋጋት ጋር ተያይዞ የመድኃኒት እጥረት ችግር መኖሩን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

“መንገዶች ወደ 14 ቀናት በመዘጋታቸው የህክምና የግብዓት እጥረቶች አሉ። በማህበረሰቡ የሚደርሰው ጥቃት አልቆመም። ግን መኪና ስለማይንቀሳቀስ የመድኃኒት ግብዓት የለም። እጃችን ላይ ያለው የተወሰነ ብቻ ነው። በተለይ ወሳኝ መድኃኒቶች ምንም የሉንም” ነው ያሉት።

ካለው የጸጥታ ስጋት አንጻር ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ተጎጂዎች የሚያክም ከፍተኛ ሀኪም እጥረት መኖሩንም አስረድተው፣ “የጸጥታ ችግሩ አልቆመም። ህዝቡ አሁንም እየቆሰለ ወደሆስፒታል እየተላከ ነው” በማለትም ገለጸዋል።

“በርካታ ቁስለኞች ወደ ህክምና ይላካሉ። በኛ ሆስፒታሉ የመጡት ብቻ ወደ 8 ይደርሳሉ። ከትላንት ወዲያ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሦስት ሰዎች ወደ ጅማ ሪፈር ተደርገዋል። እየደረሰ ያለው ጉዳት ከባድ ነው። ስፔሻሊስት ዶክተር ያስፈልጋል” ብለዋል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በበኩሉ፦
– የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ አለሚቱ ኦሞድን፣
– የክልሉን ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ማበር ኮርን፣
– የክልሉን ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ጊሎን ለምን ጥቃቱ ማስቆም እንዳልተቻለ፣ ጥቃቱን ለማስቆም ምን እየተሰራ እንደሆነ፣ “የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ጋምቤላ ክልልን ጥሰው ገብተዋል” ስለመባሉ ማብራሪያ እንዲሰጡት በተደጋጋሚ ቢሞክርም ለጊዜው ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኞች አልሆኑም።