በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች ለተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በየአመቱ በጀት ሲመደብ ነበር !

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች ለተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በየአመቱ በጀት ሲመደብ ነበር !

ፕሮጀክቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት ለሚሆን ጊዜ በየዓመቱ በጀት ሲመደብላቸው መቆየቱን የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ካቀረበለት የኦዲት ሪፖርት ያረጋገጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ጉዳዩ በአስቸኳይተመርምሮ ሪፖርት እንዲቀርብለት አዘዘ።

ሰሞኑን በሕ/ተ/ም/ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት ላይ የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲትና በኦዲቱ የተገኙ ክፍተቶችን መሠረት አድርጎ፣ ጉዳዩ ከሚመለከተው የፕላን ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጎ ነበር።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) ፥ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የክዋኔ ኦዲት ግኝትን መሠረት በማድረግ የአዋጭነት ጥናት ሳይጠና በጀት የተመደበላቸው ፕሮጀክቶች መኖራቸውን፣ የፋይናንስና የፊዚካል ሪፖርት የማያቀርቡና በተቀመጠላቸው ጊዜና በጀት ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን በመጥቀስ ሚኒስቴሩ ይህንን ለማስተካከል የወሰደውን ዕርምጃ ጠይቀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ተጠናቀው ሥራ ለጀመሩ ፕሮጀክቶች በጀት ሲመደብ መቆየቱን በመግለጽ፣ ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ ሚኒስቴሩ ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል። የፌዴራል ዋና ኦዲተር ባለፈው ዓመት የኦዲት ግኝት ሪፖርቱን ለሕ/ተ/ም/ቤት ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፣ የክዋኔ ኦዲት ካደረገባቸው ተቋማት እንዱ የፕላን ልማት ሚኒስቴር ነበር። በዚህ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ ላይም ናሙና በመውሰድ ኦዲት ካደረጋቸው የመንግሥት ፕሮጀክቶች ውስጥ በ2 ዩኒቨርሲቲዎች የተገነቡ በርካታ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ሥራ ከጀመሩ ከ1 ዓመት እስከ 3 ዓመት የቆዩ መሆናቸውን፣ ነገር ግን ለእነዚህ ፕሮጀክቶች በየዓመቱ በጀት ሲመደብ እንደነበር አረጋግጧል፡፡

የተጠቀሱት ዩኒቨርሲቲዎች ፦ ➡ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ➡ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ናቸው።

በነዚህ ሁለት ዩኒቨርሲቲዎች ከተጠናቀቁ ከ1 ዓመት እስከ 3 ዓመት ለሆናቸው ፕሮጀክቶች ከ2013 እስከ 2016 ዓ.ም. ባሉት ዓመታት ውስጥ በድምሩ 2.96 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡን፣ በጀቱም ለተባሉት ፕሮጀክቶች  አለመዋሉን የኦዲት ሪፖርቱ ይጠቁማል። ከዚህም በተጨማሪ በጀቱ ለተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች የተመደቡ መሆኑ ታውቆ ለገንዘብ ሚኒስቴር እንዲመለስ አለመደረጉ ፤ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከዩኒቨርሲቲዎቹ በተገኘ የአይቤክስ መረጃ፣ የዶክመንት ክለሳና የአካል ምልከታ መረጋገጡን ያስረዳል። በሌሎች 5 ዩኒቨርሲቲዎች ለቀረቡ ፕሮጀክቶች ደግሞ በአጠቃላይ 1.1 ቢሊዮን ብር በጀት ተለቆ እንደነበር፣ ነገር ግን የተለቀቀው በጀት ለተባሉት ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ አለመዋሉን የኦዲት ሪፖርቱ ያስረዳል። በአጠቃላይ ተጠናቀው ሥራ ለጀመሩ ፕሮጀክቶችና በጀት ተለቆላቸው ላልተከናወኑ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 4.07 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦ መገኘቱን፣ ዋና ኦዲተር በኦዲት ግኝት ሪፖርቱ አስታውቋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ምን አሉ ? የመንግሥት ፕሮጀክቶችን የመቆጣጠር ሥልጣን ለተቋማቸው በአዋጅ መሰጠቱን ጠቅሰው፣ ይህንን ተከትሎ በፕሮጀክቶች ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን ለማረም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ዋና ኦዲተር ባከናወነው ኦዲት የቀረቡ አብዛኞቹ ግኝቶች ከአዋጁ በፊት የነበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ምን አሉ ? የክዋኔ ኦዲት ግኝቱ በአዋጁ መሠረት መከናወኑን ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ምን አሉ ? በተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ላይ በጀት ሲመደብ የነበረበትን ምክንያት በሚመለከተው አካል ጥናትና ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲሰፍን በማድረግ፣ ሚኒስቴሩ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያቀርብ አሳስበዋል።