የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል፣ የኢትዮጵያው ብልጽግና ፓርቲ ደጋፊዎች ኤርትራ ከኢጋድ መውጣቷ “የመነጠል አጀንዳዋ” እና “ለበይነ መንግሥታታት መድረኮች ያላት ጥላቻ” ማሳያ ነው በማለት ላይ ይገኛሉ ሲሉ ተቹ። የማነ፣ ኾኖም ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ስትፈራረም እና ከዚያም ኢትዮጵያ ራሷ የምትቆጣጠረው የባሕር በር አጀንዳ ስታራምድ ኢጋድ ዝምታን መምረጡ፣ ለኤርትራ እና ሌሎች ተጎጂ አገራት እዳ እንዲሆን አድርጎታል በማለት ወቅሠዋል። የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊዎች ባኹኑ ወቅት በኤርትራ ላይ የማጥላላት ዘመቻ የሚያካሂዱት፣ የፓርቲውን “የራስ የባሕር በር አጀንዳ አቅጣጫ በማስቀየር የተጎጂነትና ራስን የመከላከል ዘመቻ አድርጎ ለማቅረብ ነው” በማለትም የማነ አጣጥለዋል። ለዚህ ግብ አንዱ ስልት ኤርትራን የኢትዮጵያ እና የቀጠናው “በጥባጭ” አድርጎ ማቅረብ ነው ያሉት የማነ፣ ይህ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ ግን እጅግ ይከብዳቸዋል ብለዋል።