ጥብቅና የሚቆም በሌለበትና ገዳይ “በማይታወቅበት” የቀጠለው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችን የማጽዳት ተልዕኮ አኹንም ቀጥሏል! (በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

ጥብቅና የሚቆም በሌለበትና ገዳይ “በማይታወቅበት” የቀጠለው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮችን የማጽዳት ተልዕኮ አኹንም ቀጥሏል!
(በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በኦርቶዶክስ እምነትና ንጹሓን ዜጎች ላይ የተጀመረው የማጽዳት ዘመቻ ከአርሲ ወደ ወለጋ ፊቱን በማቅናት የሆሮ ጉድሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ኤዶም ቀሲስ ዱጉማ ኡፋ እና ቀሲስ ደሳለኝ ነሞምሳ በዓል ለማክበር በወጡበት ከኅዳር 21 ጀምረው ሻምቡ መግቢያ አካባቢ ታግተው ቅዳሜ ታኅሣስ 4 ቀን 2018 ዓ.ም በአጋቾች መገደላቸውንና በአባትነት በተመላለሱበት ምድር የቀብር አፈር ተነፍገው አስከሬናቸውም እንዳልተገኘ እንዳልተቀበሩ ከቦታው ለማረጋገጥ ችለናል። አኹንም ገዳዮቹ ለላፉት 7 ዓመታት በሚገድሉብት የዳቦ ስም “ታጣቂዎች” ናቸው በሚል መሸፈኑ ነገሩን አስገራሚም ግራ አጋቢም አድርጎታል። ከቦታው በደረሰን መረጃ መሠረት ግድያውን የፈጸሙት አስከሬንም የከለከሉት በሻምቡ አካባቢ ይንቀሳቀሳል የሚባለው ኦነግ ሸኔ(ራሱን ኦነሰ ብሎ የሚጠራው) ኃይል መኾኑን ደርሰንበታል፤ በከተማ የሚኖሩ በተባባሪነትና በጥቆማም የተሳተፉ ሊኖሩ እንደሚችሉ ፍንጮች አሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያን አባቶችንና ምዕመናን ግድያ ስልታዊ በኾነ የሚፈጸም የዘር ማጽዳት ዘመቻ አካል እንጂ ድንገቴ እንዳልኾነ በጽኑ እናምናለን። እንደ ቀደሙት ግድያዎች ኹሉ በዚኽም ላይ ገዳዮችን አድኖ ፍትሕ እንዲሰፍን የሚወሰድ እርምጃ አይደለም ለሞቱ እውቅና እንኳን ያለመስጠት ብሎም ለወትሮው እንደሚደረገው የማስተባበል አዝማሚያ ነገሩ ምን ያኽል የተቀናጀና በጥንቃቄ የሚፈጸም ስለመኾኑ ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ቀሲስ ዱጉማ የ6 ልጆች አባት ሲኾኑ ቀሲስ ደሳለኝ የመንግሥት ሠራተኛና የኹለት ልጆች አባት ናቸው፡፡

በአንጻሩ ለእነዚህ በእምነታቸውና በሃይማኖታዊ ተልዕኮዋቸው ምክንያት ለተገደሉ ወገኖቻችን ጥብቅና የሚቆምና የሚከራከርላቸው አካል እንደሌለ ብናውቅም እናት ፓርቲ ይኽን ሃይ ባይ በሌለበት ኹኔታ የሚደረግን ዘር ማጽዳትና ዘር ማሳሳት በጽኑ ያወግዛል። የእምነቱ ተከታዮችም ቦታና ጊዜው ይለያይ ካልኾነ በስተቀር ይኽ ተግባር ለኹሉም የሚቀር እንዳልኾነ ተረድተው ነቅተው ራሳቸውን እንዲጠብቁ ያሳስባል።

በመጨረሻም ፓርቲያችን ለሞቱት እረፍተ ነፍስን ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸውና ለመላው የእምነቱ ተከታዮች ደግሞ መጽናናትን ይመኛል።

እናት ፓርቲ