የፎቶው ባለመብት,Getty Images
የአሜሪካ መንግሥት ከሦስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያውያን በጊዜያዊ የሕግ ከለላ በአገሪቱ ውስጥ እንዲኖሩ እንዲሠሩ የፈቀደበትን አሠራር እንዲያከትም ወስኗል።
በትግራይ ጦርነት ምክንያት በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለኢትዮጵያውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች ሲሰጥ የነበረው ጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ መነሳቱን ተከትሎ፤ ከለላው ተሰጥቷቸው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካ ለመውጣት የ60 ቀናት ጊዜ ተሰጥቷቸዋል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ክሪስቲ ኖም “የአገሪቱን ሁኔታ በመመርመር እና ከሚመለከታቸው የአሜሪካ መንግሥት አካላት ጋር በመመካከር” ኢትዮጵያ ለጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎችን “የማታሟላ አገር ናት” የሚል ውሳኔ መተላለፉን አስታውቀዋል።
በ60 ቀናት አሜሪካን ለቅቀው እንዲወጡ የተነገራቸው ኢትዮጵያዊያን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል? ጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ የሚሰጥባቸው ሁኔታዎችስ የትኞቹ ናቸው? የሚለውን በተመለከተ በአሜሪካ ከአሥር ዓመት በላይ የሠሩትን የሕግ ባለሙያ ሙሉዓለም ጌታቸው አድገህ አነጋግረናል።
ጊዜያዊ ከለላ ምንድን ነው? በምን ዓይነት ሁኔታስ ይሰጣል?
የአሜሪካ መንግሥት ጊዜያዊ ጥበቃ ወይም ከለላ መስጠት የጀመረው በአውሮፓውያኑ 1991 ሲሆን፤ ይህ መብት የሚሰጠው በአገራቸው ግጭት፣ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ ወይም ሌላ ለደኅንነታቸው አስጊ የሆነ ክስተት ለገጠማቸው ስደተኞች ነው።
Temporary Protected Status ወይም TPS ከተሰጣቸው አገራት መካከል ሶማሊያ እና ሶሪያ (ከጦርነት ጋር በተያያዘ) እንዲሁም ኤል ሳልቫዶር (ከርዕደ መሬት ጋር በተያያዘ) ይጠቀሳሉ።
ለአንዳንድ አገራት እስከ 20 ዓመት የዘለቀ ከለላ ተሰጥቷል። ለምሳሌ የሶማሊያ ጊዜያዊ ጥበቃ ከ1994 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ቆይቷል።
“እንደ ስሙ ጊዜያዊ ነው። ቋሚ እንዲሆን ታስቦ አይደለም የተዘጋጀው” ሲሉ የሕግ ባለሙያው ሙሉዓለም ጌታቸው ይገልጹታል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ለስደተኞች የሚሰጠውን ጊዜያዊ ከለላ በየጊዜው ያድሳል። ጥበቃው የሚደረግላቸው ሰዎች አሜሪካ ውስጥ የመሥራት መብት አላቸው።
ጊዜያዊ ከለላ እንደ መኖሪያ ፈቃድ ወይም እንደ ዜግነት የሚወሰድ አይደለም። በከለላው ሥር ያሉ ሰዎች የሕጋዊ ጥበቃው ቀነ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ ከአሜሪካ መውጣት ወይም ለሌላ ዓይነት የስደተኞች/ጥገኝነት ጠያቂዎች ከለላ ማመልከት አለባቸው።
የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ሕጋዊ ጥበቃ በመጀመሪያ ለ18 ወራት ተግባራዊ እንዲሆን ለኢትዮጵያውያን መስጠት የጀመረው ጥቅምት 11/2015 ዓ. ም. ነው።
በወቅቱ በዋነኛነት የትግራይ ጦርነትን ጨምሮ በአገሪቱ ውስጥ ውስጥ የነበረውን የትጥቅ ግጭት፣ የተለየ እና ጊዜያዊ ሁኔታን ከግምት በማስገባት በአሜሪካ ውስጥ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኙ ተፈቅዶ ላለፉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል።
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ጊዜያዊ ከለላ ሥር ከተካተቱት መካከል አገራት ሄይቲ፣ ቬንዙዌላ፣ አፍጋኒስታን፣ ካሜሩን፣ ሱዳን፣ ዩክሬን፣ ኤል ሳልቫዶር፣ ሆንዱራስ፣ ኒካራጉዋ ይገኙበታል። ከዚህ ቀደም ላይቤሪያ፣ ቦስኒያ-ኸርሴጎቪና እና ኩዌት ጥበቃ ተሰጥቷቸው ነበር።
ለኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረው ጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላ
የሕግ ባለሙያው ሙሉዓለም እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ የተካተተችው በታኅሣሥ 12/2022 ሲሆን ከለላው ተሰጥቶ የነበረው ከአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2022 በፊት ወደ አሜሪካ ለገቡ ሰዎች ነው።
ይህንን ፈቃድ የቀድሞው የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለ18 ወራት አራዝሞት የነበረ ሲሆን፤ የከለላው ቀነ ገደብ የተጠናቀቀው ታኅሣሥ 12/2025 ነው።
“ይህ ማለት ከታኅሣሥ 12 ጀምሮ ያልቃል ማለት አይደለም። የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እንደገለጸው የሚያበቃው የካቲት 12/2026 ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።
በዚህም መሠረት በጊዜያዊ ጥበቃ ሥር ያሉ በቀጣይ 60 ቀናት ውስጥ ከአሜሪካ እንዲወጡ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል። ከዚያ በኋላ የሚቆዩ ሰዎች “ከከለላ ውጭ” እንደሚሆኑም የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ።
አምስት ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን እና ከኢትዮጵያ የሄዱ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎች በዚህ ከለላ ሥር እንደነበሩ ተገልጿል።
በጥበቃው ሥር ተካትተው የነበሩት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ መዳረሻቸው ኢትዮጵያ የሆነ (ኢትዮጵያ ቆይተው አሜሪካ የገቡ) የተለያየ አገር ዜጎችም ጭምር ናቸው።
“ፓስፖርታቸው የኢትዮጵያ ባይሆንም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ለአደጋ እንዳይጋለጡ ከለላ ይሰጣቸዋል” ይላሉ ባለሙያው።
ጊዜያዊ መቆያው የሥራ ፈቃድን ስለሚያካትት ለስድስት ወይም ለ18 ወራት አልያም ደግሞ ለሁለት ዓመት መሥራት ይችላሉ።
የሕግ ባለሙያ ሙሉዓለም እንደሚሉት በቀጥታ በጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ ሥር ብቻ የነበሩ እና በሌላ የስደተኞች/ጥገኝነት ጠያቂዎች ከለላ ሥር ያልተካተቱ ኢትዮጵያውያን “በግምት 1000” ቢሆኑ ነው።
አምስት ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በዚህ ከለላ ሥር እንዳሉ ቢነገርም አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ከጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ በተጨማሪ ሌሎችም የከለላ አሠራሮች ሥር የተካተቱ ናቸው።
በጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ ሥር ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር “ብዙ የሚባል አይደለም” ሲሉም ያስረዳሉ።
ለማነጻጸሪያነት፤ ከሶማሊያ ከለላው የተሰጣቸው ሰዎች እስከ 700 ሺህ፣ ከቬንዙዌላ እስከ 600 ሺህ እና ከሄይቲ እስከ 500 ሺህ ይደርሳሉ።
የፎቶው ባለመብት,Getty Images
በጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ ሥር ሆነው የተማሪዎች ቪዛ (ኤፍ1) ወይም ሌላ ከለላ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ የሚጠቅሱት ባለሙያው “ቲፒኤስን የሚፈልጉት ጊዜያቸው ሲያልቅ [ወደ አገር ቤት] ላለመመለስ እና ለሥራ ፈቃድ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።
በጊዜያዊ የሕግ ጥበቃ ሥር በአንድ ወር ውስጥ አመልክቶ የሥራ ፈቃድ ማግኘት ይቻላል። ከሌሎች ከለላዎች በተሻለ ፈጣን የሥራ ፈቃድ ማግኛ መንገድ ሲሆን፣ ገደብ የሌለው የሥራ ፈቃድ በመሆኑም በማንኛውም የሥራ ዘርፍ መሰማራት ይቻላል።
ይህ ጊዜያዊ ሕጋዊ ጥበቃ ለኢትዮጵያውያን በተፈቀደበት ጊዜ ወደ 27 ሺህ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር በወቅቱ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ገልጾ ነበር።
የዚህ ጥበቃ ተጠቃሚ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ውሳኔው ይፋ ከመሆኑ በፊት በአሜሪካ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ የቆዩ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን፣ ከተጠቀሰው ጊዜ በኋላ ወደ አሜሪካ መግባት ለዕድሉ ተጠቃሚ እንደማያደርግ ተግልጾ ነበር።
ከሌሎች የስደተኞች ጥበቃዎች በምን ይለያል?
ኢትዮጵያውያን ከለላውን ለማግኘት ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ መሄዳቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር።
ከጥቅምት 2022 በፊት ወደ አሜሪካ ለገቡ ሰዎች ከለላው ይሰጥ የነበረ ሲሆን፤ ሕጋዊ ጥበቃው ባለበት እንዲጸና በዚህ ወቅት ወደ አሜሪካ ከገቡ በኋላ በተከታታይ አሜሪካ ውስጥ መኖር ግዴታቸው ነው።
ለምሳሌ ወደ ኢትዮጵያ ወይም ወደ ሌላ አገር ከተጓዙ ከለላው እንደሚቋረጥ የሕግ ባለሙያው ያብራራሉ።
ከጥቅምት 2022 በፊት አሜሪካ ከገቡ ሰዎች በተጨማሪ ከሚያዝያ 11/2024 በፊት አሜሪካ ለገቡ የተሰጠ ከለላ እንዳለ የጠቀሱት ባለሙያው፤ እነዚህ ሰዎችም ከአሜሪካ ሳይወጡ መኖር እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
“ከለላው ኢትዮጵያ፤ ከኢትዮጵያ ለሚመጡ ሰዎች አደገኛ ናት ብሎ መንግሥት የሚሰጠው ነው። legal notice [ሕጋዊ ማሳሰቢያ] ነው” ይላሉ።
ይህ ማለት ደግሞ ከለላው የተሰጣቸው ሰዎች እንደ ሌሎች ጥገኝነት ጠያቂዎች ‘ኢትዮጵያ ብመለስ አደጋ ይደርስብኛል’ የሚለውን ማስረጃ ማቅረብ አይጠበቅባቸውም።
“መንግሥት አደገኛ ነው የሚለውን ተረድቶ የሰጠው ከለላ በመሆኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አገራቸው መመለስ ለአደጋ እንደሚያጋልጣቸው የማሳመን ሕጋዊ ግዴታ (legal burden) የለባቸውም።”
የኢትዮጵያዊያን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል?
የሕግ ባለሙያው ሙሉዓለም እንደሚሉት፤ በ60 ቀናት አሜሪካን እንዲለቅቁ የተነገራቸው ኢትዮጵያዊያን ከጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላ ውጭ ወደሆኑ የጥገኝነት መጠየቂያ አሠራሮች መዞር ይችላሉ።
“በዚህ 60 ቀን ውስጥ ወደ ጥገኝነት ወይም ወደ ሌላ ‘ስታተስ’ ጥያቄ መለወጥ ይቻላል። ነገር ግን ከለላ እንደሚያስፈልጋቸው ለማሳየት ማስረጃ ማቅረብ ግዴታቸው ነው።”
የሚያቀርቡት ማስረጃ ሐሰተኛ ከሆነ የአሜሪካን መንግሥት ማታለል ወንጀል በመሆኑ ለወደፊት ሊገኝ የሚችል የስደተኞች ከለላን እንደሚያሳጣቸው ያሰምሩበታል።
ጥገኝነት መጠየቅ ያልፈለጉ ሰዎች ከየካቲት 12/2026 በፊት ከአሜሪካ መውጣት አለባቸው።
በገዛ ፈቃዳቸው አሜሪካ ለቅቀው የሚወጡ ሰዎች አንድ ሺህ ዶላር እንደሚሰጣቸው በአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት መገለጹን በተመለከተ የሕግ ባለሙያውን ጠይቀን ይህ አሠራር ለኢትዮጵያውያን የሚተገበር አለመሆኑን አስረድተዋል።
በበጎ ፈቃዳቸው ከአሜሪካ ለመውጣት (voluntary departure) የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ደንበኞቻቸውን በተመለከተ ለአሜሪካ መንግሥት መረጃ ቢሰጡም፤ “ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፈቃደኛነት የመውጣት ስምምነት ስለሌለ ራሳቸው ትኬት ቆርጠው መሄድ አለባቸው” የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል።
አንድ ሺህ ዶላር ይሰጣል የሚለው አካሄድ “ለኢትዮጵያውያን የሚሠራ አልመሰለኝም” ሲሉም አክለዋል።
ለኢትዮጵያውያን ተሰጥቶ የነበረው ጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላ መነሳቱን በተመለከ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በድረ ገጹ የሰጠው ማብራሪያ ከሌሎች ጥበቃው ከተነሳባቸው አገራት የተለየ ይዘት የለውም።
“ለሁሉም አገራት የተሰጠው ከለላ መነሳቱን በተመሳሳይ መንገድ ነው የገለጹት” ሲሉ የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ።
ለኢትዮጵያውያን ሕጋዊ ከለላው የተሰጠው በትግራይ ጦርነት ወቅት እንደሆነ ጠቅሰው “አሁንም በሌሎች ቦታዎች ጦርነቶች አሉ” በማለት የተጋረጠውን አደጋ ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያውያን ሊኖራቸውን የሚችለው አንደኛው የሕግ አማራጭ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ የከፋ ሆኗል፤ በ60 ቀናት ውጡ መባሉ ትክክል አይደለም ብለው በፍርድ ቤት መክሰስ ነው።
“ወደ ክስ ቢሄዱ [ከአሜሪካ መውጣቱን] ለጥቂት ወራት ሊያራዝመው ይችላል” ይላሉ የሕግ ባለሙያው።
ሌላኛው አማራጭ መንግሥት አንድ ሺህ ዶላር እንደሚሰጥ ቢያስታውቅም ተግባራዊ አልሆነም በሚለው መክሰስ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
“መንግሥት አታሎናል፤ አንድ ሺ ዶላር አልሰጠንም ብለው ፍርድ ቤት ሊወስዱት ይችላሉ።”
ጊዜያዊ ሕጋዊ ከለላቸው በመነሳቱ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ከወሰዱ አገራት መካከል ሶሪያ እና ቬንዙዌላ ይጠቀሳሉ።
የቬንዙዌላ ከለላ መነሳቱ ትክክል አይደለም በሚል በታች ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተመልክቶት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ውሳኔውን የማስተላለፍ ሥልጣን አለው ሲል በይኗል።
በሌላ በኩል ደግሞ ለሶሪያ የተሰጠው ከለላ ለተጨማሪ ቀናት/ወራት እንዲራዘም ተወስኗል።