በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ካህናት እንዴት ተገደሉ?

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ አቅራቢያ ህዳር 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ከቤተክርስቲያን አገልግሎት በሚመለሱበት ወቅት በታጠቁ አካላት ተይዘው ከተወሰዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን አገልጋዮች መካከል ሁለት ካህናት ተገደሉ፡፡

ከታገቱ ከሁለት ሳምንታት ግድም በኋላ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ታህሳስ 04 ቀን 2018 ዓ.ም. መገደላቸው ይፋ የሆነው የአገረስብከቱ ስራአስከያጅ እና አንድ ሌላ አገልጋይ የታገቱት በዞኑ በጅማ ገነቲ ወረዳ የምትገኝ ቀዲዳ ማሪያም ቤተክርስቲያን አገልግሎት ውለው ወደ ሻምቡ ከተማ በምመለሱበት ወቅት በመንገድ ላይ ባደፈጡ ታጣቂዎች እንደሆነ የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡

በእለቱ ህዳር 21 ቀን 2018 ዓ.ም. ወደ ጅማ-ገነቲ ወረዳ ሀራቶ ከተማ ቀዲዳ ማሪያም ለአገልግሎት ተጉዘው የነበሩት የሀገረስብከቱ አገልጋዮች ላይ እገታው የተፈጸመው ጬካ-አባጀና በሚባል ደናማ ስፍራ ነው ተብሏል፡፡ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሥር በምትገኘው ሐረቶ ማርያም በዓሉን አክብረው ሲመለሱ ከነበሩት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች መካከል የሀሮሮጉዱሩ ሀገረስብከት ስራአስከያጅ መልአከ ኤዶም ቀሲስ ዱጉማ ዱፋ እና ሌላው የቤተክስቲያን አገልጋይ ቀሲስ ደሳለኝ ነሞምሳ ቅዳሜ ዕለት መገደላቸው ተረጋግጧልም ተብሏል::

እገታው እንዴት ተፈጸመ?

በእለቱ በታጣቂዎች ተገድለዋል ከተባሉት ሁለቱ ካህናት ጋር ከአገልግሎት ስመለሱ የነበሩና በታጣቂዎች እገታ ወቅት በዚያው የነበሩ አንድ ለደህንነታቸው ስባል ግን ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡት የአይን እማኝ ለዶይቼ ቬለ እንደነገሩት፤ እገታው የተፈጸመባቸው በአገረስብከቱ ተሽከርካሪ ወደ ሻምቡ ከተማ በመጓዝ ላይ ሳሉ ነበር፡፡ “በእለቱ ከታገቱት መካከል እኔ አንዱ ነበርኩ” ያሉን የአይን እማኙ በርካቶች ያመለጥነው ታጣቂዎች ወደ ሚፈልጉት አቅጣጫ ከመጓዝ ይልቅ አከባቢው ላይ ወዳለው የበቆሎ ማሳ ገብተው እንደተደበቁና ከእገታው እንዳመለጡ ገልጸዋል፡፡

“በእገታው ወቅት ስንጓዝበት የነበርነው የአገረስብከቱ ፕካፕ ተሽከርካሪ ላይ ወደ 20 የሚሆኑ የቤተክስቲያን አገልጋዮች ነበርን” ያሉት ከእገታው ያመለጡ የአይን እማኝ፤ ታጣቂዎቹ በወቅቱ ሁለቱን ካህናት ከሌሎች ሁለት ወጣቶች ጋር ከለዩዋቸው በኋላ አንድ ላይ አራት ሰዎችን ብቻ ይዘው ወደ ጫካ መጓዛቸውን አክለው አስረድተዋል፡፡

የካህናቱ ግድያው መሰማት…

በእለቱ እገታው ከቀኑ ከዘጠን እስከ አስር ሰዓት ግድም በጠራራ ጸሃይ መፈጸሙን የገለጹልን የአይን እማኙ ያልተጠበቀ ያሉት የካህናቱ ግድያ ቅዳሜ ማታውን በመረጋገጡ ትናንት ምዕመናን እና ቤተሰቦች እርማቸውን እንዲያወጡ መደረጉንም አከለው ገልጸዋል፡፡ “እኛ እንግዲህ ታጣቂዎቹ ይለቁአቸዋል የሚል እምነት ነው የነበረን” በማለትም ሁለት ሳምንታት ካቆዩአቸው በኋላ ሁለቱን ታጋቾች ለቀው ሁለቱን ካህናት ግን “ሰውተውአቸዋል” ብለዋል፡፡ “ሀዘኑ ቤተክርስቲያን ላይ የመጣ ከባድ ሀዘን ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪው የአይን እማኝ፤ አብሮአቸው መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ የነበሩ የጓደኞቻቸው ግድያ መሪር ሀዘን ማኖሩንም ነው የገለጹት፡፡ “የአገልጋዮቹ ሞት በመረጋገጡ ብለቀስም አስከሬናቸውን አግኝተው ስርዓተ ቀብር መፈጸም ግን አልተቻለም” ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

ኦሮምያ ክልል
ኦሮምያ ክልልምስል፦ Seyoum Getu/DW

ግድያው የፈጠረው ስጋት

ሌላው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የአገረስብከቱ አገልጋይ ጥቃቱን አሳሳቢ ሲሉ ገልጸውታል፡፡ “በህዳር 21 የተደረገው ነገር በጣም አሳዛኝ ነው” በማለት የሁለቱ ካህናት ግድያ አሳዛኝም አሳሳቢም ነው ብለውታል፡፡ አገልጋዮቹ ግድያ አሳሳቢ ነው ያሉት የቤተክርስቲያን አገልጋይ ባልደረቦቻቸው በአስተያየታቸው በዚህ ገድያ ከታጣቂዎች ጋር በመስራት የተጠረጠሩ ሰባት ሰዎች በመንግስት የፀጥታ አካላት ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ነው በአስተያየታቸው የገለጹት፡፡ ዶይቼ ቬለ በዚህ ጉዳይ ላይከሆሮ ጉዱሩ ወለጋዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሚሬሳ ፊጤ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለዛሬ አልተሳካም፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከዚህ በፊት በአርሲ ዞን በተደጋጋሚ ምዕመኖቿ ላይ ያነጣጠረ ተደጋጋሚ ጥቃቶች መፈጸማቸውን በማሳወቅ ጥበቃም እንዲደረግ ለመንግስት ጥሪ ማቅረቧ አይዘነጋም፡፡