ነውረኛው ብልፅግና ቡድን በጉልበት ስራ የተሰማሩ ወጣቶችን አፍኖ “የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች” በሚል ሐሰተኛ መረጃ እያሰራጨ መሆኑ ታውቋል።
ከጉልበት ሰራተኞች በተጨማሪ የባጃጅ አስከርካሪዎችንና የሊስትሮ ባለሙያዎችን በማፈን ነው የሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳው ሰለባ ያደረጋቸው።
አገዛዙ እስረኞችን ሰብስቦ “የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች” በሚል በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ሰልፍ ሊያካሂድ መሆኑን ነው የመረብ ሚዲያ ምንጮች የገለፁት።
አገዛዙ በተለይ በደብረማርቆስ ከተማ በርካታ ቁጥር ያላቸው በጉልበት ስራና በሌሎች የስራ መስኮች ተሰማርተው የነበሩ ወጣቶች አፍኖ ወደ ባህርዳር የወሰዳቸው ሲሆን፡ በተመሣሣይ በሌሎች ከተሞችም ወጣቶችን እያፈነ ሊያካሂድ ላሰበው የሰልፍ ትርኢት እያዘጋጃቸው መሆኑ ታውቋል።
በየከተማው በገፍ እየታፈሱ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ተከታታይነት ያለው መድሀኒት የሚወስዱና የአዕምሮ ሕሙማን ጭምር እንደሚገኙበት ነው ጣቢያችን መረብ ሚዲያ ካሰባሰበው መረጃ ለማረጋገጥ የቻለው።
የብሔራዊ ተሐድሶ ኮሚሽን “እጅ የሚሰጡ የፋኖ አመራሮችንና አባሎችን በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የሰልፍ ትርኢት በማድረግ ለማሳየት እቅድ መያዙን ጣቢያችን ከሰሞኑ መዘገቡ አይዘነጋም።
የተሐድሶ ኮሚሽኑ፡ እጅ የሰጡ ታጣቂዎች በሚል ሰልፍ ለማካሄድ እቅድ ይዞ የነበረው ሰሞኑን እነማስረሻ ሰጤ እጃቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ብዙ ኃይል እናመጣለን ያሉትን ተማምኖ ነው ተብሏል።
ነገር ግን እነማስረሻ እናመጣለን ያሉትን ኃይል ማምጣት ባለመቻላቸው “እጅ ይሰጣሉ ያላችኋቸው የፋኖ አመራሮች እስካሁን ለምን አልሰጡም?” በሚል ኮሚሽኑ እነማስረሻ ሰጤን በደብዳቤ ጠይቋል።
የተሐድሶ ኮሚሽኑ፡ እነ ማስረሻ “አባሎቻችን ይመጣሉ” ባሉበት ቀን ባለማምጣታቸው የሰልፍ ፕሮግራሙ እንደተጓተተበት ገልፆ፡ “በአጭር ቀናት ውስጥ እንዲመጡ አስደርጉ” ሲል በምክትል ኮሚሽነሩ ብርጋዲየር ጄነራል ደርቤ መኩሪያ የተፈረመበት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለነማስረሻ መሰጠቱን መረብ ሚዲያ ከሁለት ቀናት በፊት መዘገቡ ይታወሳል።
በሆዳቸው ወድቀው የሕልውና ትግሉንና ታላቁን የአማራ ሕዝብን የካዱት ባንዳዎቹ እነ ማስረሻ ሰጤና መስፍን፡ ወደሚያውቋቸው ፋኖዎች ስልክ እየደወሉ “አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባለሦስት መኝታ ክፍል ያለው ኮንድሚኒየም ቤት እናሰጣችኋለን፡ ከግማሽ ሚሊየን ጀምሮ የስራ መንቀሳቀሻ ገንዘብ ለእያንዳንዱ ሰው ተመድቧል” በሚል ለማማለል እየሞከሩ ቢሆንም፡ ነገር ግን አፍንጫችሁን ላሱ የሚል ምላሽ ተሰቷቸዋል።
እነማስረሻ ይመጣሉ ያሏቸው የፋኖ አመራሮችና አባሎች በመቅረታቸው አገዛዙ የሰልፍ ትርኢቱ ከሚስተጓጎልብኝ በሚል ወጣቶችን ከየመንገዱ፣ ከየ መዝናኛ ማዕከሉ፣ ከየስራ ገበታቸውና ከትምህርት ቤቱ በግዳጅ እያፈሰ “የሰላም አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች” በሚል ሐሰተኛ መረጃ እያሰራጨ መሆኑን ነው መረብ ሚዲያ ለማረጋገጥ የቻለው።