ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጋር “ተጨማሪ ውይይት” እንደማይደረግ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ላለፉት 13 ዓመታት የተደረጉ ውይይቶች “አንዳችም መፍትሔ” አላመጡም ብለዋል።
የሕዳሴ ግድቡ ከተመረቀ በኋላ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ያለው ግንኙነት “የበለጠ መሻከሩን” ጠቅሰው፤ በዚህ መካረር ምክንያት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “ስጋት ሊሰማው” እንደሚገባም ተናግረዋል።
ባለፉት 13 ዓመታት በአገራቱ መካከል የተደረገው ውይይት ውጤት ባለማስገኘቱ፤ ግብፅ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት “የውሃ ደኅንነቷን እንደምታስከብር” አክለዋል።
ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ጋር የተደረጉ ውይይቶች ምንም ውጤት ባለማስገኘታቸው “በቀጣይም ንግግር ማድረግ አስፈላጊ አይደለም” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
የግድቡ ጉዳይ “ከኢትዮጵያጋር ካለን የሁለትዮች ግንኙነት ጋር የሚያያዝ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ግድቡን “እንደተናጠል እርምጃ ነው የምንቆጥረው” ብለዋል። አክለውም “ሕገ ወጥ ነው” ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
ግድቡን “ከዓለም አቀፍ ሕግ ጋር የሚጣጣም አይደለም” ሲሉ የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ “ዓለም አቀፍ ሕግ በግልጽ እንደሚለው ማንኛውም ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ በዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች መመራት አለበት። ይህም ማለት ማሳወቅን እና ጉዳት አለማስከተሉን ማረጋገጥ ያስፈልጋል” በማለት አብራርተዋል።
ከአንድ ወር በፊት ግብፅ ብሔራዊ ጥቅሟን እና የውሃ ደኅንነቷን ለማስጠበቅ “አስፈላጊ የሆኑ ሁሉንም እርምጃዎች እንደምትወስድ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ መናገራቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በሰጠችው ምላሽ፤ ግብፅ “ሕገ ወጥነት እና የበላይነት በተሞላው መንገድ” የዓባይ ወንዝን ለመቆጣጠር መሞከሯን ቀጥላለች ብላለች።
አል ሲሲ፤ ግብፅ በዲፕሎማሲ እና እንደ መንግሥታቱ ድርጅት ባሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ መተማመኗ እንደ ድክመት መቆጠር የለበትም ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ፤ ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በማስተዳደር ረገድ እየተከተለች ያለውን “ኃላፊነት የጎደለው” አካሄድ አገራቸው “እጇን አጣጥፋ አትመለከትም” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሰጠው ምለሽ፤ “ኢትዮጵያ በዓባይ የመጠቀም መብቷን አሳልፋ እንደማትሰጥ” አስረግጧል። “ከኢትዮጵያ ጠላቶች በኩል በእጅ አዙር ጫና ቢበረታም” የኢትዮጵያ ዕድገት “አይቀለበስም” ሲልም አክሏል።
ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ፤ የሕዳሴ ግድቡ “ከዓለም አቀፍ ሕግ ውጭ የተወሰደ የአንድ ወገን እርምጃ ነው። ይህም የሚያሳዝን ነው። እኛን ስላላማከሩን ዕውቅና አንሰጠውም” ብለዋል።
ያሳለፍነው መስከረም ወር ማገባደጃ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ሲካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት “በታችኛው ተፋሰስ የሚኖሩ የሚሊዮኖችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥላለች” ብለው በመክሰስ አገራቸው ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ትወስዳለች ብለው ነበር።
በዚያው ጉባዔ ላይ የተገኙት በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ ተወካይ ዮሴፍ ካሳዬ ለግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጡት ምላሽ፤ “ግብፅ ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ያደረገችው ንግግር መሠረት አልባ እና አሳሳች ነው” ሲሉ አጣጥለዋል።
ግብፅ “ስለ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተዓማኒ ያልሆኑ ክሶችን በተደጋጋሚ ወደ ተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አቅርባለች” ሲሉም አክለዋል።
የሕዳሴ ግድቡ ከተመረቀ በኋላ ግድቡ “በአግባቡ ባለመተዳደሩ ምክንያት የተለቀቀው ውሃ በሱዳን ጎርፍ አስከትሏል” በሚል ግብፅ ክስ አቅርባ ነበር።
ኢትዮጵያ ክሱን አስተባብላ፤ የግብፅ ክስ “ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳሳት” እንዲሁም “ሐሰተኛ የተጎጂነት ትርክት ለመፍጠር ያለመ” እንደሆነ ገልጻለች።
ከግብፅ ክስ በተቃራኒው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ባይኖር ኖሮ ባለፉት ወራት በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች የታየው “ከፍተኛ ዝናብ”፤ “ሱዳን እና ግብፅ ውስጥ በሰው ሕይወት እና በመሠረተ ልማት ላይ ታሪካዊ ውድመት ሊያመጣ ይችል” እንደነበረም የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገልጿል።
13 ዓመታት የቆየው ድርድር
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር “ምንም ስምምነት ላይ ሳንደርስ ከ13 ዓመታት በላይ ስንደራደር ቆይተናል። እኛ በቅን ልቦና ስንደራደር ስለነበረ የሚያሳዝን ነው” ብለዋል።
አያይዘውም፤ “ሌላኛው ወገን ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ይህንን የድርድር ጊዜ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ለመቀየር ተጠቅሞበታል” ሲሉ ከስሰዋል።
“የድርድሩ ሒደት ወደፊት ሊቀጥል የማይችልበት ነጥብ ላይ ደርሷል ብለን ከአንድ ዓመት በፊት በግልፅ አሳውቀናል” በማለትም በቀጣይ የሚካሄዱ ውይይቶች እንደማይኖሩ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት “ባለበት ቆሟል” ያሉት ሚኒስትሩ “[ግድቡ] ጉዳት የሚያደርስብን ከሆነ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ብሔራዊ ጥቅማችንን እና የውሃ ደኅንነታችንን የመጠበቅ ሙሉ መብታችንን እንጠቀማለን” ብለዋል።
ባለፈው ጥቅምት አጋማሽ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተካሄደው የአውሮፓ ኅብረት እና ግብፅ ጉባኤ በኋላ የወጣ መግለጫ፤ የአውሮፓ ኅብረት፤ ግብፅ ካለባት “የውሃ እጥረት” የተነሳ “በናይል ወንዝ ላይ በከፍተኛ መጠን ጥገኛ መሆኗን እንደሚገነዘብ” ጠቅሷል።
“የግብፅን የውሃ ደኅንነት እና ዓለም አቀፍ ሕግን ማክበርን” በተመለከተ ለካይሮ ያለውን ድጋፍ የገለጸው የአውሮፓ ኅብረት፤ ይህ አቋሙ “የኢትዮጵያን ግድብም እንደሚያካትት” አስታውቋል።
በብራሰልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፤ የአውሮፓ ኅብረት ከግብፅ ጋር በመሆን ካይሮ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታነሳውን “የቅኝ ግዛት እና የብቸኛ ተቆጣጣሪነት መብት የሚያስተጋባ” መግለጫ አውጥቷል በማለት መውቀሱ ይታወሳል።
የአውሮፓ ኅብረት እና ግብፅ ያወጡት የጋራ መግለጫ፤ “በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ፣ አድልዎ ያለበት እና ጠበኛ አቋም” ያሳየ እንደሆነ በመግለጽም ተቃውሞውን አሰምቷል።
ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ “በናይል ተፋሰስ ውስጥ ከሚገኙ አገራት መካከል 98 በመቶ የሚሆነውን ውሃ ከናይል በማግኘት ግብፅ የወንዙ ጥገኛ የሆነች ብቸኛዋ አገር ነች” ብለዋል።
“ሌላ የውሃ ምንጭ የለንም” ያሉት ሚኒስትሩ ከናይል ወንዝ በየዓመቱ “55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ” እንደሚያገኙ እና ግብፅ የምትጠቀመው ዓመታዊ የውሃ መጠን ግን “ከ80 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ” እንደሆነ ጠቅሰዋል።
“ስለዚህ ባለን ውሃ እና በፍላጎታችን መካከል ያለውን ክፍተት የምናሟላው ውሃውን በድጋሚ ጥቅም ላይ በማዋል ነው። በዓለም ላይ አራት ጊዜ ውሃን እንደገና ጥቅም ላይ የምታውል ብቸኛ አገር ነን” ሲሉም አክለዋል።
የፎቶው ባለመብት,Reuters
ግብፅ በቀጣይ ምን ታደርጋለች?
በዓለማችን በርዝመቱ የሚታወቀው የዓባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ ውሃውን የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ነው።
የወንዙን አብዛኛውን ውሃ የምትጠቀመው ግብፅ፤ በኢትዮጵያ ግድብ መገንባቱ የውሃ መጠን ይቀንስብኛል ስትል በተደጋጋሚ ከስሳለች። ኢትዮጵያ ይሄንን ውንጀላ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።
የግብፁ ሚኒስትር በበኩላቸው “ከውሃ አንጻር ከድህነት ወለል በታች ነን። በተባበሩት መንግሥታት [መርኅ] መሠረት የድህነት ወለሉ በነፍስ ወከፍ 1,000 ኪዩቢክ ሜትር ነው። የግብፅ የነፍስ ወከፍ ድርሻ 500 ኪዩቢክ ሜትር ነው። ውሃ ከሌለ ሥልጣኔ፣ ፒራሚዶችም፣ ምንም አይኖርም” ብለዋል።
ግብፅ በቀጣይ ምን ልታደርግ እንደምትችል የተጠየቁት ሚኒስትሩ “በዓለም አቀፍ ሕግ እና በተባበሩት መንግሥታት ስምምነት ላይ በመመሥረት” እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የውይይት በር ክፍት መሆኑን ገልጻለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው “ለ13 ዓመታት ተነጋግረን ምንም ነገር ላይ አልደረስንም። ምንም መግባባት ላይ አልደረስንም። ስለዚህ፣ በዚህ ማለቂያ በሌለው መንገድ በመቀጠል ሌላኛው ወገን መሬት ላይ ያሉ ነገሮችን እንዲቀይር ዕድል አንሰጥም” ብለዋል።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስተዳደር እና የውሃ ሙሌት ላይ ለዓመታት ድርድር አድርገዋል። ሆኖም ሁሉንም የሚያስማማ መቋጫ ላይ ሳይደርሱ የግድቡ ግንባታ ተጠናቅቆ ሥራ ጀምሯል።
ግብፅ በአፍሪካ ግዙፉ የሆነውን ግድብ ጉዳይ ባለፉት ዓመታት ለተባበሩት መንግሥታት፣ ለአፍሪካ ኅብረት እና ለአረብ ሊግ በማቅረብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ሞክራለች።
“የፀጥታው ምክር ቤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና ደኅንነትን የሚመለከት ዋና መድረክ ስለሆነ እና ይህ ጉዳይም ግልጽ የሆነ የዓለም አቀፍ ደኅንነት እና ሰላም ስጋት ስለሆነ ወደ ምክር ቤቱ ያመራል” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በየካቲት 2020 በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ በዓለም ባንክ እና በአሜሪካ ግምጃ ቤት ሽምግልና ከስምምነት ተደርሶ እንደነበርም በመጥቀስ ግብፅ ብትስማማም ኢትዮጵያ ለመፈረም ሳትስማማ ቀርታለች ብለዋለ።
“[ስምምነቱ] ለእኛ የሚስማማ አልነበረም። ነገር ግን ለግብፅ፣ ለሱዳን እና ለኢትዮጵያ የተሻለ አማራጭ ነበር። በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን ለፊርማው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ አቅንተው ነበር። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን የኢትዮጵያው ሚኒስትር አልተገኙም” ሲሉ ወቅሰዋል።
ግብፅ በሶማሊያ ጦር ማሰማራቷ ኢትዮጵያን ያሰጋታል?
በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ያለው ውጥረት ሲባባስ በአንጻሩ በሶማሊያ እና በግብፅ መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከሩ ይታወሳል።
በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመው ወታደራዊ ስምምነት ተግባራዊ ሆኖ የግብፅ ሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ የጦር ጄነራሎችን እና መሣሪያዎችን ይዘው ማረፋቸው ይታወሳል። የግብፅ ጦር በሶማሊያ መሬት መስፈሩ በኢትዮጵያ ዘንድ በበጎ አልታየም።
ግብፅ በበኩሏ፤ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮን (አትሚስ) የሚተካው አዲስ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰማሩ 10 ሺህ ወታደሮችን ለማሰማራት ዕቅድ መያዟን አስታውቃለች።
የግብፅ ሠራዊት በሶማሊያ መሰማራቱ ከኢትዮጵያ ጋር ካለው ውጥረት ጋር የሚገናኝ ስለመሆኑ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ የተጠየቁት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ “የማይመሳሰሉ ነገሮችን መቀላቀለ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“ሶማሊያ አሸባሪዎችን እንድታሸንፍ ለመርዳት በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ውስጥ እየተሳተፍን ነው። እኛ ከሶማሊያ እና ከአፍሪካ ኅብረት በቀረበልን ጥያቄ መሠረት ነው የተሰማራነው” ብለዋል።
ከኢትዮጵያ በኩል ስለሚነሳው ስጋት በድጋሚ ተጠይቀው “…በግልጽ እንነጋገር። በአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የፀጥታ ምክር ቤት ተጠይቀን እንዲሁም ከሶማሊያ መንግሥት በጽሑፍ በቀረበ ጥያቄ ነው የተሰማራነው። የሶማሊያን የግዛት አንድነት እና ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ እንዲሁም አልሻባብ እና ሌሎች የሽብርተኛ ድርጅቶችን ለመከላከል እንድንረዳቸው ጥሪ አቀርበዋል” ሲሉ መልሰዋል።