ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብን ሰውራዋል የተባሉ በርካታ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች ባለቤቶች እና ተባባሪዎቻቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
ተቋሙ እንዳለው ግለሰቦቹ ለመንግሥት ገቢ መሆን የነበረበትን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰወር ወንጀል ተጠርጥረው ነወ የተያዙት።
በተወሰደው እርምጃ በደኅንነት አገለግሎቱ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የ24 የስፖርት አወራራጅ ድርጅት ባለቤቶች እና ተባባሪዎቻቸው መሆናቸው ተገለጿል።
የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር ተብለው ከሚጠሩ የፋይናንስ ሥርዓቶችን ከሚያካሂዱላቸው የአገር ውስጥ የክፍያ ሥርዓት አቅራቢ ተቋማት ጋር በመመሳጠር የገንዘብ ስወራውን ፈጽመዋል ተብሏል።
ፊንቴክ ወይም አግሪጌተር የሚባሉት የአገር ውስጥ የገንዘብ ክፍያ ሥርዓት አቅራቢ ተቋማቱ ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በመውሰድ የሚንቀሳቀሱ ናቸው።
እነዚህ ድርጅቶች የደንበኛን ምሥጢር መጠበቅ የሚል ሙያዊ አሠራርን “እንደ ሽፋን ተጠቅመው” የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች የሚያንቀሳቅሱትን ገንዘብ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ደብቀዋል ወይንም አሳንሰው አቅርበዋል ተብሏል።
የብሔራዊ መረጃ እና የደኅንነት አገልግሎት በዚህ የተነሳ የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች “በግብር ስወራ እንዲሁም ከፍተኛ የአገር ሀብትን ወደ ውጭ በማሸሽ ወንጀል ላይ ተሳትፎ እንዳላቸው” አመልክቷል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የፀጥታ አካላት ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር ለማዋል በጋራ መሥራታቸውም ተገልጿል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ፈቃድ ኖሯቸው ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በገቡት ውል መሠረት የማይሠሩ፣ በሕገ ወጥ ድርጊት ተሰማርተው በመገኘታቸው ፈቃዳቸው የተሰረዘባቸው መሆኑን ጠቅሷል።
እንዲሁም ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳይኖራቸው በስፖርት አወራራጅነት ተሰማርተው የነበሩ አካላት በዓለም አቀፍ የኢንተርኔት ትስስር አማካይነት በሕገ ወጥ ድርጊት ተሰማርተው መገኘታቸውን ገልጿል።
በሕጋዊነት ፈቃድ ያወጡት ድርጅቶች ክትትል በሚደረግበት ወቅት ፈቃድ ሲያወጡ ካስመዘገቡት ቢሮ ለቅቀው መሰወራቸውንም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
መግለጫው አክሎም የቤቲንግ የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶቹ በተለያዩ የገንዘብ ክፍያ ሥርዓቶች አማካይነት የሚሰበስቡትን እና የሚያዘዋውሩትን የገንዘብ መጠን መሠረት ያደረገ ግብር አለመክፈላቸው እንደተደረሰበት ገልጿል።
በክሪፕቶከረንሲ እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሃዋላ ገንዘብ ማስተላላፊያ አማራጮች አማካኝነት የሚያገኙትን ገቢ በውጭ ምንዛሪ በመቀየር ሲሰውሩ እንዲሁም ከአገር እንዲወጣ ሲያደርጉ ቆይተዋል ሲል መግለጫው ጨምሮ አስታውቋል።
የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ጭምር ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው አገር ውስጥ ለሚገኙ ተባባሪዎቻችው ውክልና በመስጠት ሕገ ወጥ ድርጊቱን ሲፈጸሙ መቆየታቸው የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት በመግለጫው አመልክቷል።
ውጭ አገር የተዘጋጁ ሶፍትዌሮች ጥቅም ላይ ውለዋል ያለው መግለጫው፣ ድርጅቶቹ ቋሚ አድራሻ የሌላቸው መሆኑ ወንጀሉን ውስብስብና ለቁጥጥር አስቸጋሪ አድርጎት መቆየቱን ገልጿል።
በሕገ ወጥ ድርጊቱ ከአገር ሲሸሽ የነበረው ከፍተኛ ገንዘብ ሽብርተኝነትንና ፀረ ሰላም ቡድኖችን በገንዘብ ለመደገፍ፤ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ ለማስመሰል እንዲሁም ለኮንትሮባንድ ንግድ ማካሄጃ እንደሚውል ጨምሮ አስታውቋል።
ይህ ድርጊት አገራዊ ምጣኔ ሀብትን የሚቃረን እና የብሔራዊ ደኅንነትን እንዲሁም ጥቅሞችን ስጋት ላይ ለመጣል የሚደረግ እንቅስቃሴ አካል ነው ሲል የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በመግለጫው ላይ አመልክቷል።