በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ጅማ አርጆ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት አንድ ዐቃቤ ሕግ ሲገደል፣ ሦስት የሕግ ባለሙያዎች ደግሞ ታግተው መወሰዳቸውን የኦሮሚያ ዐቃቢያን ሕግ ማኅበር አስታወቀ።
ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ አንድ ባልደረባ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ድርጊቱ የተፈጸመው ረቡዕ ኅዳር 17/2018 ዓ.ም. ከሰዓት ጅማ አርጆ ወረዳ፣ ሐራ ቀበሌ ውስጥ ነው።
ታግተው ከተወሰዱት መካከል አንድ ሾፌር እንደሚገኝበት ግለሰቡ ጨምረው ገልጸዋል።
ዐቃቢያን ሕጎቹ ላይ በታጣቂዎቹ ጥቃት የተፈጸመባቸው ለሥራ ወደ ጅማ ያቀኑ በነበረበት ወቅት ነው።
“ሥራቸውን አጠናቀው በበደሌ አልፈው ረቡዕ ወደ 9 ሰዓት አካባቢ ወደ ነቀምት ሲመለሱ ታጣቂዎች መኪናቸውን አስቁመው አግተው እንደወሰዷቸው ነው የሰማነው። የታገቱት አሽከርካሪውን ጨምሮ 5 ሰዎች ናቸው።”
ግለሰቡ አክለውም ከታገቱት ግለሰቦች ጋር አብረው የነበሩትን አቶ ነገሰ ከበደ የተባሉትን ዐቃቤ ሕግ ታጣቂዎቹ መገደላቸውን ተናግረዋል።
የሕግ ባለሙያዎቹ ላይ ጥቃት አድርሰው ግድያውን እና ያገታውን የፈጸሙት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች መሆናችውን ግለሰቡ አክለው ገልፀዋል።
በኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ የሕግ አርቃቂ የነበሩት አቶ ነገሰ በታጣቂዎቹ ከዋናው መንገድ ረዥም ርቀት ለሁለት ሰዓታት በእግር ከወሰዷቸው በኋላ እንደተገደሉ ግለሰቡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከታገቱት ግለሰቦች ጋር አብረው የነበሩት አቶ ነገሰ ከበደ የተባሉ ዐቃቤ ሕግ በታጣቂዎቹ መገደላቸው ተሰምቷል
ግለሰቦቹ ለሕግ ጥናት ወደ ጅማ መሄዳቸውን የተናገሩት ግለሰቡ “የክልል፣ የአገርም ሆነ የዓለም አቀፍ ሕጎች እንደሚመሰክሩት ዐቃቢያን ሕግ የፓርቲ አባል መሆን አይችሉም። ለሕገ መንግሥቱ ነው ተገዢ የሚሆኑት። አጋቾቹ ይህን ሊገነዘቡ ይገባል። ነገር ግን እነዚህ የሕግ ባለሙያዎች ባልተገባ ሁኔታ ነው ዒላማ የተደረጉት” ብለዋል።
የግለሰቦቹ ሥራቸው የሕግ ጥናት ማካሄድ ነው ያሉት የኦሮሚያ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ባልደረባው “ለዚህ ሥራም ነበር ወደ ጅማ የሄዱት። ይህን ከግምት በማስገባት አጋቾቹ እንዲለቋቸው እንጠይቃለን” ሲሉ ተማጽኖ አቅርበዋል።
በታጣቂዎቹ የተገደሉት አቶ ነገሰ ከበደ ከሌሎቹ ባለደረቦቻቸው ተለየተው በታጣቂዎቹ ለምን ዒላማ እንደተደረጉ የታወቀ ነገር እንደሌለ የሕግ ባለሙያው ተናግረዋል።
“ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ አልነበራቸውም። ሥራቸውን ብቻ የሚሠሩ ተግባቢ እና ታታሪ ሰው ነበሩ። የሚያስገድላቸው ምንም ጉዳይ አልነበረም። የልጆች አባት ነበሩ።”
ከዚህ ቀደም በክልሉ ዐቃቢያነ ሕጎች በተመሳሳይ በተደጋጋሚ ታግተው እንደነበረ የሕግ ባለሙያው ጠቀሰው “ከፖለቲካ ነጻ መሆናቸው ሲታወቅ ግን ይለቀቃሉ። ግድያ ሲፈጸም እስከማውቀው ይህ የመጀመሪያው ነው” ብለዋል።
በታጣቂዎቹ ታግተው የተወሰዱት ዐቃቢያነ ሕጎች ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ ከተለያዩ ወገኖች ከሚሰሙት መረጃ ውጪ በእርግጠኝነት እንደማያውቁ፤ ነገር ግን በጥሩ ሁኔታ እንዳሉ ሰምተዋል።
“ብዙ መረጃ የለንም፤ ነገር ግን ከአካባቢው ሰዎች እንደሰማነው እስከሁን በመልካም ሁኔታ እንደሚገኙ ነው። ዐቃቢያነ ሕጎቹ ከታገቱ እና ከተገደሉ ሥራችን ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ ሰው ለመኖርም ስጋት ይፈጥርብናል።”
የሟች ዐቃቤ ሕግ አስክሬን ከነቀምት ወደ አዲስ አበባ እየተወሰደ እንደሚገኝ እና ነገ [አርብ] የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እንደሚፈጸም ተገልጿል።
ግለሰቡ የታገቱት ባልደረቦቻቸው ሥራቸው ከፓርቲ ነጻ እንደሆነ በመጥቀስ እንዲለለቁም ተማጽነዋል።
የአሮሞ ነጻነት ሠራዊት ቃል አቀባይ አቶ ጂሬኛ ጉደታ በቅርቡ ከግድያ እና እገታ ጋር በተያያዘ ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ድርጅታችን ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ አያደርግም” ሲሉ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ከሚፈጸሙ የሰላማዊ ሰዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የመንግሥት ሠራተኞች ግድያ እንዲሁም ጥቃቶች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።