የኢትዮጵያ ጫት በሶማሊያ ገበያ ውስጥ እንዴት ተፈላጊ ለመሆን ቻለ?

በሐረርጌ እና በዙሪያዋ ላሉ አርሶ አደሮች ጫት ዋነኛ የገቢ ምንጭ ነው። ጫትን ከማምረት አንስቶ ወደ ውጭ አገራት እስከመላክ ባለው ሒደት ውስጥ የሚሳተፉ በርካቶች ናቸው።

በአካባቢው ጫት የውጭ ምንዛሬ ምንጭም ነው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ፍተሻ የሚደረግባቸው ጣቢያዎች ቁጥር እንዲሁም እነዚህን የፍተሻ ጣቢያዎች ለማለፍ የሚጠየቀው የክፍያ መጠን ጨምሯል በሚል የጫት አምራቾች እያማረሩ ነው።

ጃፋር በአወዳይ የጫት አምራች ነው። ለዓመታት አርሶ አደሮችን ሲያማርሩ የቆዩ ችግሮች አሁንም ድረስ እንዳልተቀረፉ ይናገራል።

“ከዚህ ቀደም አርሶ አደሮችን ያማረረው ጫትን በሌላ ሰብል የመተካት ጉዳይ ነበር። ገበያው ላይ ያለው የጫት መጠን ከፍ ሲል ዋጋው ይቀንሳል” በማለት ያለውን ሁኔታ ይገልጻል።

አሁን ላይ ግን “በአገራችን የጫት ዋጋ ጨምሯል” ይላል ጃፋር።

“በአገራችን የጫት ዋጋ ጨምሯል። ለዚህ ምክንያቱ አሁን ጫት የሚበቅልበት ወቅት መሆኑ ነው። አርሶ አደሩ ጫት እየተከለ ነው። ምርቱ ሲጨምር ዋጋው ይቀንሳል።”

የጫት አርሶ አደሮች በዋነኛነት ቅሬታ ያቀርቡ የነበረው በተለያዩ ከተማዎች እና የፍተሻ ጣቢያዎች ‘የኮቴ’ ክፍያ በመጠየቃቸው ነው።

የጫት ገበያ

ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፤ በሶማሊያ ገበያ የኬንያ ጫት አቅርቦት በ17 በመቶ ቀንሷል። ስለዚህም ለኢትዮጵያ ጫት ያለው ፍላጎት ከፍ ብሏል።

ከዚህ ቀደም በሶማሊያ ውስጥ የኬንያ ጫት ተቆጣጥሮት በነበረውን ገበያ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ጫት ቀዳሚ ሆኖ ይዞታል።

በሶማሊያ ገበያ የኢትዮጵያ ጫት ተፈላጊነቱ መጨመሩን ተከትሎ፤ ኬንያ ከሶማሊያ ውጭ ያሉ የገበያ አማራጮችን እየፈለገች እንደሆነ የአገሪቱ የግብርና እና ምግብ ባለሥልጣን አስታውቋል።

አወዳይ ከተማ የተወለደው የጫት ነጋዴ አብዱልጀባር ኢብራሒም እንደሚለው፤ ኬላ ላይ ያለው ክፍያ የሚፈጥረው ችግር ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ መሰናክል ሆኖባቸው ቀጥሏል።

አብዱልጀባር ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ጫት ከሚልኩ ነጋዴዎች አንዱ ነው።

በሶማሊያ ገበያ ላይ ከኬንያ ጫት በበለጠ የኢትዮጵያ ጫት ተፈላጊ የሆነባቸው ሁለት ምክንያቶች እንዳሉ ይናገራል።

“ለምሳሌ፤ በሐርጌሳ የኢትዮጵያ ጫት በአንድ ዶላር ሲሸጥ የኬንያ ጫት በሦስት ዶላር ይሸጣል። የኢትዮጵያ ጫት በሐርጌሳ ተወዳዳሪ እንዳይሆን ከገበያው አስወጥተውታል” ይላል።

ከሦስት ዓመታት በላይ በዚህ መንገድ እንደቀጠሉ ይገልጻል።

“በዚህ ጉዳይ ስንከራከር ቆይተናል። ዋጋው ወደ አምስት ዶላር ከፍ እንዲል ጠይቀናል። አሁን የኢትዮጵያ ጫት ከኬንያ ጫት እኩል ይወዳደራል” ይላል።

ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸው እና ጫት በድብቅ ወደ ሶማሊያ መግባቱ የኢትዮጵያ ጫት ገበያውን እንዲቆጣጠር ማድረጉንም ያክላል።

ሆኖም ግን ጫት በሕገ ወጥ መንገድ መግባቱ ነጋዴዎችን ለኪሳራ እንደሚዳርግ እና ብሔራዊ ገቢን እንደሚቀንስ ገልጿል።

“ሕገ ወጥ ጫት የሚያስገቡት ሰዎች ሁሌም ችግር ውስጥ ናቸው። መንገድ ላይ ለማምለጥ ሲሞክሩ ጫቱ ይጎዳል። ጫቱ በሕገ ወጥ መንገድ መግባት አልነበረበትም። እዚያ ሲገቡ ጫቱ ተጎድቶ ነው የሚደርሱት። ስለዚህም ዋጋውን ያጣል” ይላል ነጋዴው።

ጫት በሕገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ ነጋዴዎችን ብቻ ሳይሆን አገሪቱ የምታገኘውን ጥቅምም እንደሚጎዳ ጠቅሷል።

“ጫት በሕጋዊ መንገድ ወደ ሶማሊያ ለማስገባት በየኬላው ከፍተኛ ገንዘብ ነው የምንከፍለው። በኦሮሚያ ክልል እና በሶማሌ ክልልም እንከፍላለን። ሌሎችም ክፍያዎች አሉ።”

የጫት ነጋዴዎችን ቅሬታ ተከትሎ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች ያሉ ኬላዎች እንዲነሱ የፌደራል መንግሥት ማዘዙን ነጋዴው ገልጿል።

ሌላው ጫት ኤክስፖርት የሚያደርገው ነጋዴ መሐመድ ኢብራሒም እንደሚናገረው፤ በክፍያ ጣቢያዎች ያለው የክፍያ ሥርዓት ባይሻሻልም የጫት ንግድን ለማሻሻል የተሠራው ሥራ የአወዳይ ከተማን የጫት ገበያ እንዲያድግ አስችሏል።

“በአወዳይ ከተማ መንግሥት የጫት ማዕከል ተከፍቷል። በዚህ ማዕከል ነጋዴዎች እና አርሶ አደሮች በነጻነት እየተገበያዩ ነው። ይህም የጫት ገበያን አሻሽሏል” ይላል።

በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል ስላለው የክፍያ ሥርዓት ችግር መንግሥት ምላሽ አልሰጠም። ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።