አንድ የአሜሪካ የፌደራል ፍርድ ቤት፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ 2 ሺሕ 200 የአሜሪካ ዓለማቀፍ የተራድዖ ድርጅት (ዩ ኤስ ኤ አይ ዲ) ሠራተኞች ሥራ እንዲያቆሙ ያስተላለፉት ትዕዛዝ እስከ የካቲት 7 ተፈጻሚ እንዳይኾን አግዷል።
ፍርድ ቤቱ እግዱን ያስተላለፈው፣ ኹለት የአሜሪካ የሠራተኛ ማኅበራት ፕሬዝዳንቱ ሕገመንግሥቱን እየጣሱና የድርጅቱ ሠራተኞች በፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ሳቢያ ለጉዳት እየተጋለጡ መኾኑን በመጥቀስ ያቀረቡትን አቤቱታ በመቀበል ነው።
ፍርድ ቤቱ ደመወዛቸው እየተከፈላቸው በግዳጅ ዕረፍት እንዲወጡ የተደረጉ 500 የድርጅቱ ሠራተኞችም ለጊዜው ወደ ሥራ እንዲመለሱ አዟል።
ፍርድ ቤቱ፣ የድርጅቱ ሠራተኞች በግዳጅ ዕረፍት እንዲወጡ የተላለፈው ትዕዛዝ ለረጅም ጊዜ ታግዶ እንዲቆይ የቀረበለትን አቤቱታም በቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ ይሰማል።
የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ድርጅቱን ሙሉ ለሙሉ የማፍረስ ዕቅድ እንዳለው ይነገራል።