አሜሪካ በዓለም ዙሪያ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የምትሠጠው ድጋፍ በቀጣዮቹ 5 ዓመታት እንደገና ካልቀጠለና ሌሎች ድጋፎች ካልተገኙ፣ በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በ400 ፐርሰንት እንደሚጨምርና 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች እንደሚሞቱ የተመድ የኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ድርጅት (ዩ ኤን ኤድስ) ትናንት አስጠንቅቋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ የውጭ ዕርዳታ እንዲቆም ካዘዙ በኋላ፣ እገዳው የኤች አይ ቪ በሽታን ጨምሮ ለነፍስ አድን የሚውሉ ድጋፎችን እንደማይመለከት መመርያ ተላልፎ ነበር።
ኾኖም ይህ መመሪያ ኤች አይ ቪ ኤድስን በማኅበረሰብ ደረጃ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ላይ እንዴት እንደሚተገበር አኹንም ብዥታ እንዳለ ድርጅቱ አስታውቋል።
የፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ነፍስ አድንን አመለከትም ቢባልም፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት በአሜሪካ ድጋፍ በኤች አይ ቪና ሌሎች የነፍስ አድን ሥራዎች ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች ሥራቸውን እንዳቆሙ ናቸው።