የአይ ኤም ኤፍ ( IMF )ዋና ዳይሬክተር በአዲስ አበባ

በኢትዮጵያ የኹለት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ የገቡት የዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ዛሬ ከገንዘብ ሚንስትር አሕመድ ሽዴ፣ ከብሄራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱና ከፕላንና ልማት ሚንስትር ፍጹም አሠፋ ጋር በኦአገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር አተገባበር ዙሪያ ተወያይተዋል።

ጆርጄዬቫ፣ ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል እና ብርሃን የዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤትንም ጎብኝተዋል።

ጆርጂዬቫ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጋር ጭምር እንደሚነጋገሩ፣ ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ጋር እንደሚወያዩም ገንዘብ ሚንስቴር አስታውቋል።

ጆርጂዬቫ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፣ ድርጅቱ ባለፈው ሐምሌ ለኢትዮጵያ ባጸደቀው የ3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ብድር ዙሪያ ኹለተኛውን ዙር ግምገማ በማጽደቅ ከብድሩ ውስጥ 248 ሚሊዮን ዶላር በለቀቀ ማግስት ነው።