ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ኡጋንዳ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ከሆኑት ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ ለሚመጡ ሰዎች የስደተኝነት ምዝገባ ማቆሟን አስታወቀች።
የኡጋንዳ እርዳታ፣ የአደጋ ዝግጁነት እና የስደተኞች ሚኒስትር ሂላሪ ኦኔክ እንደተናገሩት ሠራተኞቻቸው ከሦስቱ አገራት የሚመጡ ስደተኞችን እንዳይመዘገቡ ማዘዛቸውን እና ለዚህም ምክንያቱ “በአገራቱ ውስጥ ድጋፍ ስለሌለ” መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ የሚኒስቴሩ ውሳኔ የተሰማው ወደ ኡጋንዳ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በጨመረበት እና ከለጋሾች ለስደተኞች ተብሎ የሚመጣው ድጋፍ በመቀነሱ እንደሆነ የኡጋንዳ ዘ ዴይሊ ሞኒተር ዘግቧል።
ቀደም ባሉት ዓመታት ከሦስቱ አገራት የሚወጡ ስደተኞች መዳረሻ ኬንያ የነበረች ሲሆን፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ኡጋንዳን የተሻለች አድርገው በመምረጣቸው በርካታ ስደተኞች ከኢትዮጵያ፣ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ ወደ አገሪቱ እየገቡ ነው።
የአሁኑ የእገዳ ወሳኔ አዲስ የሚመጡ ሰደተኞችን የሚመለከት እንጂ ቀደም ሲል ወደ ኡጋንዳ በመግባት የተመዘገቡትን የሦስቱን አገራት ሴጎች የሚመለከት እንዳዳልሆነ ተገልጿል።
ሚኒስትሩ እስካሁን ወደ ኡጋንዳ የገቡት ስደተኞች ቁጥር ወደ ሁለት ሚሊዮን እየደረሰ አና በየዕለቱ እየጨመረ መሆኑን አመልክተው፤ በየቀኑ “በአንድ መቶ እና በ200 መካከል የሚቆጠሩ ሰደተኞች ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ብቻ” ወደ ኡጋንዳ ይገባሉ” ብለዋል።
ኡጋንዳን በበርካታ ስደተኞች ተመራጭ የሆነችው ስደተኞች በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ፣ በሥራ እና በንግድ አንዲሰማሩ ከመፍቀዷ በተጨማሪ ለዜጎች የተፈቀዱ አገልግሎቶች መጠቀም ስለሚችሉ ነው።
ሚኒስትሩ እንዳሉት ኡጋንዳ ስደተኞችን ለመደገፍ በየዓመቱ ሁለት ቢሊዮን ሽልንግ (የኡጋንዳ ገንዘብ) ታወጣለች።
አሁን ኡጋንዳ እንዳይመዘገቡ እገዳ የጣለችባቸው የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ እና የሶማሊያ ስደተኞች በዋናነት በፖለቲካዊ ምክንያቶች፣ በጦርነት እና የአገራቸውን መንግሥታት እና ሌሎች ኃይሎችን በመስጋት ነው የሚሰደዱት።
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ጊዜ በኡጋንዳ ውስጥ ከ56 ሺህ በላይ ኤርትራውያን፣ ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ ሶማሊያውያን እና 16 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ።
በቅርቡ የኬንያ መንግሥት ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ወደ ግዛቱ የሚገቡ ስደተኞችን ምዝገባ የማቆም ውሳኔ ቢያሳልፍም የስደተኞች እና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ውሳኔውን በመቃወም በመንግሥት ላይ ክስ ከፍተው በፍርድ ቤት አሳግደውታል።