የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር፣ የኢትዮጵያው ገዥ ብልጽግና ፓርቲ በባሕር በር ዙሪያ መግለጫዎችን በማውጣት ኢትዮጵያን የቀይ ባሕር ቁልፍ ባለድርሻ እንድትሆን የሚያደርገው ሙከራ “የማይሳካ”ነው ሲል አጣጥሏል። ሚንስቴሩ፣ ለኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት የሚቀርቡት “የኢኮኖሚ አስገዳጅነት”፣ “የደኅነት” እና “የታሪክ” መከራከሪያዎች የማያዛልቁ ናቸው ብሏል። ሚንስቴሩ፣ ኢትዮጵያ የአፋርን ሕዝብ ማንነት በመጥቀስ፣ በኤርትራ ሉዓላዊ የባሕር ዳርቻ ላይ የተፈጥሮ መብት አለኝ ለማለት ትፈልጋለች በማለት ተችቷል። የሁለት አገር ሕዝቦች ዝምድና የባሕር በር ለመቆጣጠር በማስረጃነት ቢወሠድ ኖሮ ኦጋዴንም ወደ ሶማሊያ ሊጠቃለል ይችላል ያለው ሚንስቴሩ፣ የኢትዮጵያ የቆዳ ስፋትም የባሕር በር ባለቤትነት ሊያጎናጽፋት አይችልም በማለት ሞግቷል። ሚንስቴሩ፣ ኤርትራ ነጻ አገር የኾነችው ኢትዮጵያን የባሕር በር ለማሳጣት አልባ ለማድረግ ነው የሚለው መከራከሪያም፣ ሐሰተኛ እና ትርጉም አልባ ነው በማለት ተችቷል።