ቢቢሲ አማርኛ በአማራ ክልል በፋኖ እና በአገዛዙ ጦር መካከል እየተካሄደ ያለውን ውጊያ ተከትሎ በመከላከያ ሰራዊት አባላት በህዝቡ ላይ የሚደርሱ ግፎችን ፣ በወታደር የሚደፈሩ ሴቶችን እንዲሁም በግፍ የሚረሸኑ ወጣቶችን አስመልክቶ ዝርዝር ዘገባ አውጥቷል።
በዘገባውም የባለታሪኮችን ስምና ማንነታቸውን የሚገልጹ ነገሮችን ለደህንነታቸው ሲል መቀየሩን አሳውቋል።
ታሪኩ እንዲህ ይጀምራል እናት እሁድ ጠዋት ወታደሮች ወደ ቤቷ ሲመጡ ከስምንት ዓመት የእህቷ ልጅ ጋር እንደነበረች ትናገራለች።
መከላከያው ታኅሣሥ 27/2017 ዓ.ም የቤት ለቤት ፍተሻ እያደረገ ነበር።
እናት የመከላከያ ሠራዊት የደንብ ልብስ የለበሱ ሦስት ወታደሮች ደቡብ ጎንደር ወደ ሚገኘው ቤታቸው እንደመጡ እና ስለማንነቷ እንዲሁም ፋኖዎች ከምትሠራበት ጠላ ቤት እንደሚመጡ መጠየቅ መጀመራቸውን ትናገራለች።
የ21 ዓመቷ እናት ፋኖዎች እንደሚመጡ ማረጋገጧን ትገልፃለች።
“እንዴት ብለን እንዋሻለን? እንዴት ብለን እንክዳለን?” የምትለው እናት ነገሮች ወዲያው ብዙም ሳይቆዩ ተካረሩ ትላለች።
ስለቤተሰቦቿ ማንነት ከጠየቋት በኋላ እናት ወታደሮቹ በአፀያፊ ቃላት እንደሰደቧት ትናገራለች። ከዚያም ሕፃኗ ማልቀስ ስትጀምር በመሣሪያቸው እንዳስፈራሯት ታስታውሳለች።
እናት ከዚያም አንደኛው ወታደር በሌሎች ወታደሮች እርዳታ በእህቷ ልጅ ፊት እንደደፈራት ተናግራለች።
“እንዳይጎዱኝ ተማፀንኳቸው። ታቦታትን እየጠራሁ ለመንኳቸው። ግን ልባቸው አልራራልኝም። አበላሹኝ።”
እናት ብቻዋን አይደለችም፤ እናት የአማራ ክልል የትጥቅ እንቅስቃሴ ከተቀሰቀሰ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል ተብሎ ከሚታመኑ በሺህዎች ከሚቆጠሩ ሴቶች ውስጥ አንዷ ናት።
ምንም እንኳ እውነተኛው ግጭት ነክ የወሲባዊ ጥቃት መጠን ሪፖርት ባለመደጉ እና ባለመርመሩ በትክክል ባይታወቅም፤ ቢቢሲ ያሰባሰበው መረጃ ከሐምሌ 2015 እስከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ድረስ ከስምንት ዓመት እስከ 65 ዓመት ዕድሜ ያላቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው ያመለክታል።
ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን በክልሉ ያለውን ግጭት ለመዘገብ በተጣለባቸው ክልከላ እና ገደብ ምክንያት ወደ ክልሉ መግባት ባይችሉም የቢቢሲ የናይሮቢ ጋዜጠኞች ቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ተጎጂዎችን እና የጤና ባለሙያዎችን በማነጋገር ቀውሱ በሰብዓዊነት ላይ እያሳረፈ ያለውን ጠባሳ የሚመለከት መረጃ አግኝቷል።
እናት የጥቃቱ ሰለባ ከመሆኗ በፊት በቤተሰቧ ውስጥ እንዳሉ ሌሎች ሴቶች ሁሉ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት አስተምህሮ መሠረት በተክሊል የማግባት ዕቅድ ነበራት።
“ከዚያች ቀን በፊት ወንድ አላውቅም ነበር” ትላለች።
“አበላሽተውኝ ሄዱ። ቢገድሉኝ ይሻል ነበር።”
የ18 ዓመቷ ትዕግሥት የምዕራብ ጎጃም ነዋሪ ስትሆን የመድፈር ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት በቤተሰቦቿ ሻይ ቤት ትሠራ ነበር።
ጥር 2016 ዓ.ም. ‘ሻይ ቡና’ ለማለት የሚመጣ ወታደር ተደጋጋሚ ጉንተላ ሲያደርስባት፤ “ሥነ ሥርዓት ያዝ” በሚል የሰጠችው ምላሽ ለደረሰባት ጥቃት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ታምናለች።
“‘ቆይ አሳይሻለሁ’ ብሎ ዝቶብኝ ወጣ።”
ምሽት አካባቢ ከሥራ ወደ ቤት ስትመለስ ትዕግሥት ቀን ላይ የጎንተላትን ጨምሮ ሦስት ወታደሮች መንገድ ላይ አድፍጠው እንደጠበቋት እና መንገድ ዳር በደቦ እንደደፈሯት ተናግራለች።
“ቤተሰቦቼ ስቆይባቸው እኔን ፍለጋ ሲወጡ መንገድ ዳር ወድቄ አገኙኝ” ስትል ታስታውሳለች ትዕግሥት።
“አፋፍሰው ወደ ጤና ጣቢያ ወሰዱኝ። እዚያም አምስት ቀን ቆየሁ።”
ጥቃቱ ከተፈጸመባት ጊዜ አንስቶ ትዕግሥት በሰዎች እና በውጭው ዓለም ፍርሃት ተሸብባ ከቤቷ መውጣት እንደማትችል ትናገራለች።
“ፍርሃት ስላደረብኝ ሥራውንም ተውኩት። . . . ወታደሮችን ሳይ በጣም እፈራለሁ። ወንዶችንም ሳይ ፍርሃት ያድርብኛል፤ እሸሻለሁ” ትላለች ጥቃቱ ከደረሰባት ከዓመት በኋላ።
ትዕግሥት የምታውቀው ሕይወት እንዴት እንደተመሰቃቀለ ስትገልፅ ከእጮኛዋ ጋር መለያየቷን እና ምን እንደተፈጠረ ምክንያቷን እንዳልነገረችው ትገልፃለች።
በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጠችው ትዕግሥት ራሷን ለማጥፋት ብትሞክርም ቤተሰቦቿ በጊዜ ደርሰው አትርፈዋታል። ከዚህ ጊዜ በኋላ ትዕግሥት በተደጋጋሚ ራሷን ለማጥፋት አስባ እንደነበር ሳትደብቅ፤ ነገር ግን ለቤተሰቦቿ ራሷን ለማጥፋት በድጋሚ እንደማትሞክር ቃል መግባቷን ተናግራለች።
ቢቢቢ በአማራ ክልል ስለተፈጠረው ቀውስ መረጃ ለማግኘት 4 በመቶ ከሆኑት የክልሉ 43 ጤና ጣቢያዎች እና የሕክምና ምንጮች መረጃዎች መሰብሰቡን ይገልጻል
በእነዚህ ተቋማት ከሐምሌ 18/2015 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ድረስ 2,697 ሰዎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው ሪፖርት አድርገዋል። ከእነዚህም ውስጥ 45 በመቶ የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ናቸው።
ከተጎጂዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በደረሰባቸው ጥቃት በአባላዘር በሽታ ሲያዙ፤ በርካቶች ደግሞ ለእርግዝና እና ለከባድ የሥነ ልቦና ቀውስ ተዳርገዋል።
ይሁን እንጂ በርካታ የወሲባዊ ጥቃት ተጎጂዎች መገለልን በመፍራት፣ የአባላዘር በሽታ መያዛቸውን ወይም መፀነሳቸውን ላለማወቅ የተፈፀመባቸውን የመደፈር ጥቃት ሪፖርት ማድረግም ሆነ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አይፈልጉም።
ለዚህም ነው በደኅንነት ስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ከፍተኛ የጤና ባለሙያ በአማራ ክልል ግጭት ወደ ጤና ተቋማት የመጡ ተጎጂዎች “ከባሕሩ በጭልፋ ናቸው” የሚሉት።
ለምለም እንደ ኤችአይቪ ዓይነት በሽታ ተላልፎብኝ ሊሆን ይችላል በሚል ስጋት የተፈፀመባትን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ሪፖርት ካላደረጉት እና የሕክምና እርዳታ ካላገኙ ተጎጂዎች መካከል ናት።
የ23 ዓመቷ የደቡብ ጎንደር ነዋሪ ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም. የመንግሥት ወታደሮች በተለመደ እንቅስቃሴያቸው “መሣሪያ ያለውን ሠው ጠቁሚን ብለው” መረጃ ፍለጋ ወደ ቤታቸው መምጣታቸውን ትናገራለች።
የሚፈልጉትን መረጃ ባለመስጠቷ አንደኛው ወታደር ከዛተባት በኋላ እንደደፈራት ተናግራለች።
“‘ጩኸት ብታሰሚ አንድ ጥይት ነው የሚበቃሽ’ ብሎ አስፈራራኝ” ትላለች ለምለም።
አንድ ወር ሙሉ አለቀስኩ። ምግብ አይርበኝም። ሥራዬ ማልቀስ ብቻ ቆሜ ለመሄድም ተቸገርኩ። ሕመምተኛ ሆንኩ።”
ማኅበረሰባዊ ሐሜትን በመፍራት ጭንቀት ውስጥ መግባቷን የምትናገረው ለምለም፤ ከቤተ ክርስቲያን መራቋንም ተናግራለች።
“ሴት ሆኖ መፈጠር ያስጠላል። ወንድ ብሆን ደብድበው ጥለውኝ ይሄዳሉ እንጂ እንደዚህ ሕይወቴን አያበላሹትም ነበር” ስትል ለምለም የደረሰባት ጥቃት ቁስል በሴትነቷን ላይ ያሳደረባትን ከባድ ስሜት ታብራራለች።
“እያለቀሱ፤ በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ፤ ለማውራት እየከበዳቸው ነው የሚመጡት” ሲሉ አንድ የጤና ባለሙያ የተጎጂዎችን ስሜት ይገልፃሉ።
ሆኖም ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ተጎጂዎች የአጥቂዎቻቸውን ማንነት ለመናገር እንደሚያመነቱ እና ፍትሕን ፈልገው እንደማይመጡ ባለሙያዎች አመልክተዋል። ይህም በከፊል በግጭቱ ምክንያት ሕግ እና ሥርዓት በመስተጓጎሉ ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች ለሕክምና ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ተጎጂዎች በእርግዝና ፍርሃት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።
ሌሎች ደግሞ ጥቃቱ ከደረሰባቸው በኋላ ዘግይተው ወደ ጤና ተቋማት የመምጣት አዝማሚያ ያላቸው ሲሆን፤ ኤችአይቪን ጨምሮ የአባላዘር በበሽታዎች መከላከያ በማይሠሩበት ወቅት ይደርሳሉ።
በተለይም በጎጃም አካባቢዎች ዘግይቶ ወደ ሕክምና ተቋም የመምጣት አዝማሚያ ከፍተኛ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ተጎጂዎች አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያ (ፖስት ፒል) እንዲሁም የኤችአይቪ ቅደመ መከላከል አይወስዱም ብለዋል።
ሌላ የጤና ባለሙያ ግጭቱ ባሳደረው የትራንስፖርት መስተጓጎል እና መንገድ መዘጋት ምክንያት በርካታ ተጎጂዎች የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን እንደሚገልፁ ተናግረዋል።
የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች መከላከያ ሠራዊት ካምፕ በመሠረተባቸው እና በሚቆጣጠራቸው ከተሞች አካባቢ የተፈፀሙ ቢሆንም፤ ባለሙያዎች የከተማ ነዋሪዎች የተሻለ ግንዛቤ እና የጤና አገልግሎት ስለሚያገኙ ጥቃቶችን ሪፖርት የማድረግ አዝማሚያቸው ከፍ ያለ ነው ይላሉ።
በቢቢሲ ዘገባ መሰረት በፋኖ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎች የሉም።
የተመድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቢሮ ሰኔ 2016 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ በአገዛዙ እና በፋኖ መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሕፃናት ላይ ጨምሮ ወሲባዊ ጥቃቶች የተፈፀሙት በመከላከያ ሠራዊት ነው ብሏል።
የአፋብኃ ቴዎድሮስ እዝ ምክትል ሰብሳቢ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አስረስ ማረ ለቢቢሲ ተዋጊዎቻቸው የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ስለመፈፀማቸው እውቅ እንደሌለው እና የቀረበባቸው ክስም እንደሌለ ተናግሯል።
ምክትል ሰብሳቢው አክሎም ወሲባዊ ጥቃት የፈፀመ ተዋጊ “ያለርኅራሄ” እስከ ሞት የሚያደርስ ቅጣት የሚጥል ሕግ እንዳላቸው ገልፀዋል።