የጂንካ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ለመገናኛ ብዙሀን መረጃ መስጠታቸውን ተከትሎ ከሀላፊነታቸው ተነሱ

ዋዜማ- የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር በአካባቢው ስለተከሰተው “የሔሞሬጂክ ፊቨር” እንደሆነ በተገመተው ተላላፊ በሽታ ሰዎች መሞታቸውን ገልፀው ለመገናኛ ብዙሀን መረጃ መስጠታቸውን ተከትሎ ከሀላፊነታቸው ተነሱ።

ዋዜማ ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮና ከሆስፒታሉ ምንጮች እንደሰማችው የጂንካ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ቢንያም አስራት ለአንድ አለማቀፍ ሚዲያ “የሔሞሬጂክ ፊቨር” እንደሆነ በተገመተው በሽታ ሳቢያ ሀኪሞችን ጨምሮ ሰዎች መሞታቸውን ገልፀው መረጃ በመስጠታቸው ከሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ ምስጢሩ ሐምደኪ በተጻፈ ደብዳቤ ከሕዳር 5 ቀን 2028 ዓ.ም ከሀላፊነታቸው መነሳታቸው ተነግሯቸዋል።

ዳይሬክተሩ ከሃላፊነት ከመነሳታቸው በፊት ወደ ሆስፒታሉ መጥተው ከታከሙት አራት በሽተኞች አንዱ በህይወት እንዳለ እና የተሻለ የሚባል የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልፀው ሁለት የሆስፒታላቸው የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ እስካሁን ስድስት ሰዎች ተመሳሳይ ምልክቶችን በማሳየት ህይወታቸው ማለፉን ለዶቸ ቨለ ራዲዮ በይፋ ገልፀው ነበር።

የበሽታው ክስተትና ምንነት ዓለማቀፍ ትኩረት የሳበ ሲሆን የዓለም የጤና ድርጅትም ከመንግስት ጋር በመቀናጀት አስቸኳይ የመስክ ቡድን ወደ ስፍራው ልኳል።

የጤና ሚኒስቴር እስከአሁን ድረስ ስምንት ሰዎች በበሽታው የተጠረጠሩ መሆኑን ባወጣው መግለጫ ይፋ ያደረገ ሲሆን ስለ ሞቱ ሰዎች ያለው ነገር የለም።

ዶክተር ቢንያም አስራት በበሽታው ሞት መመዝገቡን ይፋ ካደረጉ በኋላ ዛቻ እና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነ የቅርብ የስራ ባልደረቦቻቸው ነግረውናል።

ዶ/ር ቢንያም በሆስፒታሉ ውስጥ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አስራር በማስተዋወቅና የኦክስጅን ማምረቻ ማዕከል በማስገንባት ለአገልግሎት ለማብቃት በዝግጅት ላይ እንደነበሩ ባልደረቦቻቸ ይናገራሉ።

ሆስፒታሉን በበላይነት የሚያስተዳድርው የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ በጉዳይ ላይ አስተያየት እንዳለው ብንጠይቅም ሀላፊዎቹ ምላሽ መስጠት እንደማይፈልጉ ነግረውናል።

የጤና ሚንስቴር እና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጂንካ ከተማ “ትክክለኛ ምንነቱ ገና በመጣራት ላይ ያለ እና “የሔሞሬጂክ ፊቨር” በሽታ እንደሆነ የተገመተ በሽታ መከሰቱን ሕዳር 3 በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀው ነበር።

የዓለም ጤና ድርጅት፣ የበሽታውን ምንነት ለማወቅ ለሚደረጉ ምርመራዎች እና በሽታውን ለመቆጣጠር ለሚደረጉ ጥረቶች 11 አባላት ያሉት የአስቸኳይ ድጋፍ ሰጪ ቡድን እና የሕክምና መሳሪያዎችን ወደ አካባቢው መላኩን እንዲሁም ለዚሁ ጥረት የሚውል 300 ሺሕ ዶላር መመደቡን አስታውቋል። [ዋዜማ]