በኢትዮጵያው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ይደረግ የነበረው ድርድር ባሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል

ግብጹ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ባደር አብደላቲ፣ በኢትዮጵያው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ይደረግ የነበረው ድርድር ባሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል በማለት አል-አሃር ከተባለ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ መናገራቸውን የአገሪቱ የዜና ምንጮች ዘግበዋል። አብደላቲ፣ ኢትዮጵያ ያለ ምንም ቅንጅታዊ አሠራር ግድቡን ውሃ በመሙላትም ሆነ ከግድቡ ውሃ በመልቀቅ በመጀመሪያ በሱዳን ላይ ከዚያም በግብጽ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስታደርስ ቆይታለች በማለት እንደከሰሱ ዘገባዎቹ ጠቅሰዋል። ሆኖም ይህ የኢትዮጵያ የተናጥል አካሄድ ፈጽሞ ሊቀጥል አይችልም ሲሉ አብደላቲ አስጠንቅቀዋል ተብሏል። ግብጽ በተመድ ቻርተር መሠረት የውሃ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ ሙሉ መብት እንዳላት መግለጣቸውንም የዜና ምንጮቹ ጠቅሰዋል። አብደላቲ፣ አሜሪካን ጨምሮ ዓለማቀፉ ኅብረተሰብ ግብጽ በሕዳሴ ግድብ እና በናይል ወንዝ ውሃ ላይ ስላላት አቋም በቂ መረጃ እንዳገኙ መናገራቸውን ጭምር ዘገባዎቹ ጠቅሠዋል።