ጂንካ ውስጥ እስካሁን ምንነቱ ባልታወቀ አጣዳፊ በሽታ ሁለት የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ህይወታቸው አለፈ

(መሠረት ሚድያ)- ጂንካ ከተማ ውስጥ ባለፉት ሶስት እና አራት ቀናት ውስጥ እስካሁን በምርመራ ባልተረጋገጠ አጣዳፊ በሽታ ምክንያት ስድስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ሚድያችን አረጋግጧል።

መላ የከተማውን ህዝብ ባስደነገጠው ክስተት የጂንካ  ቃለህይወት ቤተክርስቲያን አገልጋዮች እንዲሁም አንድ ዶክተር እና አንድ ነርስ በበሽታው ከተጠቁ በኋላ ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

አንድ ስሜ አይጠቀስ ያለ በጂንካ ሆስፒታል የሚሰራ የጤና ባለሙያ ክስተቱ ትክክል መሆኑን በመግለፅ አሁን ላይ ሶስት ታማሚ በሆስፒታሉ እንዳለ እና ከታማሚዎቹ ጋር ግንኙነት የነበራቸው በርካቶች እንዳሉ ጠቅሷል።

“በከፍተኛ ፍርሀት ውስጥ ነን። በሽታው መድሀኒት የሚቋቋም e-coli የተባለ ህዋስ ተገኝቶበታል። ኢቦላ ነው አይደለም የሚለው ተጨማሪ ምርመራ ይጠይቃል” ብሏል።

“ሁሉም የሞቱት መጀመሪያ ከሞተው ታማሚ ጋር ንክኪ የነበራቸው ናቸው፣ እንዲሁም በሁሉም ላይ አንድ አይነት ምልክቶች ታይተዋል፣ እና በሽታው ከሶስት እስከ አምስት ቀን ባለው ግዜ ለሞት የሚዳርግ ነው” ያሉት የጤና ባለሙያው ይህ ሁሉም በፍርሀት እንዲዋጥ አርጓል ይላሉ።

አክለውም “ለምሳሌ ታማሚውን ከዛሬ አንድ ሳምንት በፊት እያከመ የነበረው ዶክተር ነው ህይወቱ ያለፈው። በአካባቢው ሌሎችም ንክኪ ያላቸው ብዙ ሰዎች በመኖራቸው አስፈላጊ ጥንቃቄ ለማድረግ የክልሉ ጤና ቢሮ እና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስፈላጊ መረጃ ለሕዝቡ ይፋ ሊያደርጉ ይገባል” ብለዋል።

ህይወታቸው ያለፉት ሰዎች በአፋቸውና በአፍንጫቸው ደም እየፈሰሰ እንደነበር ታውቋል።

“በዚህ በሰዎች ተደጋጋሚ ሞት ምክንያት የጂንካ ከተማ ህዝብ በከፍተኛ መደናገጥ እና ሀዘን ውስጥ የገባ ሲሆን የክልሉ ጤና ቢሮና የህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩትም አካል ሁሉ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠዉ እናሳስባለን” ብለዋል።

ከሟቾቹ መሀል የአሪ ዞን ፖሊስ መምሪያ የሥራ ባልደረባ የነበሩት ኢንስፔክተር ወንድማገኝ ጨነቄ መሆናቸውን የጂንካ ፖሊስ አስታውቋል።

በዚህ ዙርያ መሠረት ሚድያ የጂንካ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ሚስጥሩ ሀምደኪን ያነጋገረ ቢሆንም የሰዎቹን መሞት ከማረጋገጥ ውጭ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን በመግለፅ ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።