የኔዘርላንድ ፓርላማ አባል የሆኑት ኢሳ ካራማን (Isa Kahraman)፣ በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል፣ በተለይም በምስራቅ አርሲ ዞን፣ በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሃይማኖት ተኮር ግድያ መንግስታቸው እንዲያጣራ በይፋ ጥያቄ አቀረቡ።
አባሉ፣ ለኔዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ቫን ዊል (David Van Weel) ባቀረቡት ደብዳቤና ተያያዥ የፓርላማ ጥያቄዎች፣ ጥቃቱ “ስልታዊ እና በተጠና መልኩ” የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው፣ በአውሮፓ ህብረት በኩል “በኦነግ ሸኔ” (OLA) እና ሌሎች ተጠያቂ ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል።
የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባል የሆኑት አቶ ኢሳ ካራማን፣ ጉዳዩን በግል እንደሚመለከቱት ገልጸዋል፡-
“በተመሳሳይ በደል ውስጥ እንዳለፈ ክርስቲያን፤ በስቃይ እና መከራ ውስጥ እያለፉ ላሉ የእምነት ወንድሞቼ መብት የመቆም ሃላፊነቴን እወጣለሁ። በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ በግሌ ይሰማኛል። ኔዘርላንድ እየተሳደዱ ያሉ ክርስቲያን ወገኖችን መርሳት የለባትም” ብለዋል።
የፓርላማ አባሉ፣ ባለፈው ህዳር ወር መጀመሪያ በምስራቅ አርሲ በ26 ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመውን ግድያ በማንሳት፣ ይህ የዘመቻው አካል መሆኑን በደብዳቤያቸው አውስተዋል።
አቶ ካራማን የኔዘርላንድ መንግስት በጉዳዩ ላይ ጠንካራ አቋም እንዲወስድ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አቅርበዋል፦
1. የመረጃ ማረጋገጫ፡ የኔዘርላንድ መንግስት በዲፕሎማሲያዊ ምንጮቹ ስለተፈጸመው ጥቃት፣ ስለተጠረጠሩት ፈጻሚዎች (በተለይ ኦነግ ሸኔ) እና ስለ ኢትዮጵያ ባለስልጣናት ምላሽ ምን መረጃ አለው?
2. ገለልተኛ ምርመራ፡ መንግስታቸው፣ የኢትዮጵያ መንግስት በግድያዎቹ ላይ “አፋጣኝ፣ ገለልተኛ እና ይፋዊ ምርመራ” እንዲያደርግ እና ወንጀለኞችን ለፍርድ እንዲያቀርብ እንዲወተውት ጠይቀዋል።
3. የማዕቀብ ጥያቄ፡ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን የማያደርግ ከሆነ፣ ኔዘርላንድ በአውሮፓ ህብረት በኩል “በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀብ አገዛዝ” (Global Human Rights Sanctions Regime) ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን እና “ኦነግ ሸኔን ጨምሮ” ሌሎች አካላትን በማዕቀብ መቅጣት የሚቻልበትን መንገድ እንዲያጤን አሳስበዋል።
4. የልማት ትብብር፡ በመጨረሻም፣ በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለው ይህ ጥቃት፣ ኔዘርላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ባላት “የልማት ትብብር እና የሰብአዊ መብት ፖሊሲ” ውስጥ እንዴት ግምት ውስጥ እንደሚገባ እና የዚህን ቡድን ጥበቃ “ግልጽ የፖሊሲ ቅድሚያ” እንዲሰጠው ጠይቀዋል።