አርበኝነት በጀግኖች መስዕዋትነት የደም ቀለም የሚከተብ ህያው የኪዳን ብራና ነው❗️
ከአፋብኃ በላይ ዘለቀ ዕዝ የተላለፈ የሀዘን መግለጫ
ከጥንት ታሪካችን ከዛሬ ተግባራችን ከራስ በላይ ለሀገር ከራስ በላይ ለህዝብ በማስቀደም በላብ ተጠምቀን ደማችን አፍሰን አጥንታችን ከስክሰን አንጡራ ንብረት አባክነን በድልና በክብር ሀገር ፀንቶ እንደቆየና ዛሬም የህዝባችን ማንነታዊ ህልው ዕጣ አስቀጣይነት አርበኝነታችን መሆኑን እንገነዘባለን።
ጥቅምት 29/2018 ዓ.ም በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ አጅሬ የተሰኘች አነስተኛ ከተማ የጠላትን የእጅ አዙር ተልዕኮ ሳያነግቡ እንዳልቀረ በተጠረጠሩ ግለሰቦች በተተኮሰ ጥይት የሰሜን አምባራስ ክ/ጦር አዛዥና የራስ አሞራው 3ኛ ኮር አስተዳደር ኃላፊ የሆነው ጀግናው አርበኛ ጌትነት መሳፍንት መስዕዋትነት ከፍሏል።
ከአስር ዓመት በላይ ከወላጅ አባቱ ከአይበገሬው አርበኛ መሳፍንት ተስፉ ጋር በመሰለፍ የለጋነት ዕድሜውን ሁሉ በአርበኝነት በላቀ ወታደራዊ ብቃት በተሻለ ፖለቲካዊ ንቃት ፍዳ የገጠመውን የአማራ ህዝብ ለመታደግ አያሌ የጦር ግንባሮችን በድል የቋጨው ጌትነት መሳፍንት በተለያዩ ግንባር ተጋድሎዎች አምስት ጊዜ ቆስሎ የነበረ ቢሆንም ከቁስሉ ሳያገግም ፍልሚያ ተመልሶ እየተሰለፈ ሲሻው በክላሽ ሲሻው በብሬን ጠላትን እየገረፈ ድል ሲነሳ ኑሯል።
ወላጅ አባቱ አርበኛ መሳፍንት ተስፉ፣አጎቱ መከተ ተስፉን፣ወንድሞቹ ሻምበል መሳፍንት፣ገብሬ መሳፍንትን ጨምሮ ከ30 በላይ ቤተሰቦቹ በነቂስ በተሰለፉበት የአስርት ዓመታት የአማራ ትግል የጨለማው ዘመን ፅልመት አለንልህ አማራ ብለው የተስፋ ጮራ ከፈነጠቁት ጀግና አርበኞች መካከል በለጋ ዕድሜያቸው የተሰለፉት ብላቴናዎች ጌትነት መሳፍንትና ሻምበል መሳፍንት እንደነበሩ ሀገር ያወቀው ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው።
አርበኛ ጌትነት መሳፍንት ተስፉ በድንገተኛ አጋጣሚ የህይወት መስዕዋትነት እስከከፈለበት ዕለት ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በቀናነትና በጀግንነት የተሰጠውን ህዝባዊ ተልዕኮ ሁሉ ሲፈፅም ቆይቷል።
ከዚህ ቀደም በርካታ ቤተዘመድ በትግል መስዕዋትነት ያጣው የምንጊዜም ወደር የለሽ ጀግና አርበኛ መሳፍንት ተስፉ የአብራኩ ክፋይ የሆኑትን ልጆቹን አርበኛ ገብሬ መሳፍንትና አርበኛ ጌትነት መሳፍንት በማጣቱ እንዲሁም የዕዛችን ጠንካራ አርበኛ ጌትነት መሳፍንት መስዕዋትነት የተሰማንን ልባዊ ሀዘን እየገለፅን
አርበኝነት በጀግኖች መስዕዋትነት የደም ቀለም የሚከተብ ህያው የኪዳን ብራና ነውና አርበኛ ጌትነት መሳፍንት ተስፉ እና ሌሎች እልፍ ጀግና አርበኞቻችን ዓላማ ግብ ለማድረስ ከመቸውም ጊዜ በላይ በብስለትና በቁርጠኝነት እንተጋለን።
ለወዳጅ ቤተ ዘመድ መፅናናቱን እንመኛለን!!
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ
ሰሜን አማራ ቀጠና በላይ ዘለቀ ዕዝ