የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የአፋር ክልላዊ መንግሥት የትግራይ ኃይሎች ወደ አፋር ክልል ዘልቀው በመግባት ጥቃት ፈጽመዋል በማለት ያሠማው ክስ “መሠረተ ቢስ ነው” በማለት ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ አጣጥሏል። አፋር ውስጥ “ሓራ መሬት” የተባለው ታጣቂ ኃይል ካሁን ቀደም በትግራይ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን መፈጸሙን የጠቀሠው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ “ችግር ፈጣሪው” የአፋር ክልላዊ መንግሥት አሁን ራሱ ከሳሽ ሆኖ ብቅ ብሏል በማለት ወቅሷል። ፌደራል መንግሥቱ የፕሪቶሪያውን የግጭት ማቆም ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉ፣ የትግራይ ሕዝብን ሥቃይ ከማራዘም አልፎ የሕዝቡን ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ሊያስተጓጉል ይችላል በማለትም ጊዜያዊ አስተዳደሩ አስጠንቅቋል።