ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ፣ ሕወሃት እና የፌደራል መንግሥት ተፈናቃዮችን የፖለቲካ መያዣ በማድረግ ለከፋ ጉስቁልና ዳርገዋል ሲል ዛሬ በሠጠው መግለጫ ወንጅሏል። የቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተስፋለም በርኸ፣ መንግሥት ከፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት ማዕቀፍ ውጪ በአፍሪካ ኅብረት የተፈናቃዮች ያካምፓላ ድንጋጌ መሠረት መመለስ እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ተስፋለም፣ በፌደራል መንግሥቱና ሕወሃት መካከል ያለው መካረር ወደ ዳግም ጦርነት እንዳያመራ ከፍተኛ ስጋት እንዳላቸው ገልጠው፣ ችግሩ “በንግግር” እና “በድርድር” እንዲፈታ ጠይቀዋል። ድርጅቱ፣ የተፈናቃዮች ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቁሟል።