ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በዶይቼ ቬለ ዘጠኝ ዘጋቢዎች ላይ የጣለውን ጊዜያዊ እገዳ ባስቸኳይ እንዲያነሳ ትናንት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። ፌዴሬሽኑ፣ ውሳኔው ጣቢያውን “ዝም ለማሠኘት” እና “በአማራ ክልል ስለሚካሄደው ግጭት ኢትዮጵያዊያን ገለልተኛ መረጃ እንዳያገኙ ለመገደብ” ያለመ ነው በማለት ተችቷል። ዶይቼ ቬለ፣ ባለሥልጣኑ የእገዳውን ምክንያት በዝርዝር ማስረጃ እንዲያስደግፍ እና ጊዜያዊውን እገዳ እንዲነሳ ከቀናት በፊት መጠየቁ ይታወሳል።