የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሲቪል ሠርቪስ ቢሮ፣ መንግሥት ከመስከረም ጀምሮ ለኹሉም መንግሥት ሠራተኞች በፈቀደው የደመወዝ ማሻሻያ መሠረት ገንዘብ ሚንስቴር የፈቀደው የ10 ወር የደመወዝ በጀት ከክልሉ ሠራተኞች ቁጥር አንጻር ሲታይ በቂ እንዳልኾነ አስታውቋል። ቢሮው፣ በክልሉ ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪ በጀት ላይ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ጉድለት እንደተፈጠረ ገልጧል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ቤንሻንጉል ጉሙዝን ጨምሮ በብዙ ክልሎች የመረጃ ክፍተት የተፈጠረው በክልሎች ወይስ በፌደራል ደረጃ ስለመኾኑ ተጣርቶ ለውሳኔ እንዲቀርብ በቅርቡ መመሪያ መስጠታቸውን የጠቀሠው ቢሮው፣ የክልሉ የፋይናንስ ቢሮም ይህንኑ የማጣራት ሥራ ጀምሯል ብሏል። ይሄው የማጣራት ሥራ ተጠናቆ መንግሥት ውሳኔ እስኪሠጥ ድረስ፣ ሠራተኞች በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ለሚናፈሱ “አሉባልታዎች” ጆሮ እንዳይሠጡ አሳስቧል።