የተቃውሞ ትችት ኃላፊነትን መወጣት እንጂ ባንዳነት አይሆንም!
ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ በፓርላማ ያቀረብኳቸው ጥያቄዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ሕይወት የሚመለከቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው። እኔ እንደ ሕዝብ ተወካይና ተቃዋሚ ፖለቲከኛነቴ፣ የመንግሥትን ሥራ መተቸትና ለሕዝብ ጥቅም መቆም ስራየም፣ ግዴታዬም ጭምር ነው።
የምመራባቸው ብቸኛ መርሆዎች የአማራ ሕዝብ ህልውናና የኢትዮጵያ ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞች ናቸው። ከዚህ በመነሳት ማክሰኞ ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረብኳቸው ጥያቄዎች ላይ የገዢው ፓርቲ የማህበራዊ ሚዲያ ሰራዊት እና ወዶ ገብ መሸጦ “ተቃዋሚዎች” ላቀረቡት ሦስት ክሶች ግልጽ ምላሽ እሰጣለሁ። ይሄን የማደርገው የተነሱት ክሶች ክብደት ምላሽ የሚገባቸው በመሆናቸው ሳይሆን አጋጣሚውን በመጠቀም ባቀረብኋቸው በርካታ የፖሊሲና የትግበራ ጉዳዮች ላይ የበለጠ ግንዛቤ እንዲፈጠር ውይይት እንዲካሄድባቸው ምልከታዎቼን በተብራራ ሁኔታ ለማጋራት ነው።
ክስ አንድ፦ የአስመራ መንግሥት ወኪል፣ አገልጋይና ባንዳ ነህ
ይህ ክስ መሰረተ-ቢስ፣ ተራ ስም ማጥፋት ነው። የፖለቲካ ትችትን በባንዳነትና በክህደት ስም ለመምታት የሚደረግ አሳፋሪ ሙከራም ነው። የቤተሰቤ ታሪክ የጀግንነት ታሪክ፣ በላብና በጥረት ሰርቶ የማደር እንጂ በመሸጦነት እና በባንዳነት የማደር አንዳችም ነገር የለበትም። አባቴ ወታደር ጫኔ ዳኜው በዘውዳዊ ስርዓቱ፣ ወንድሜ መቶ አለቃ አያሌው ጫኔ (የሀረር ጦር ት/ቤት ምሩቅ እና የነብሮ ክፍለ ጦር መኮንን) በወታደራዊ ደርግ ዘመን፣ እንዲሁም ሌላው ወንድሜ ተስፋሚካኤል ጫኔ (የሁርሶ ወታደራዊ ት/ቤት አሠልጣኝ) በኢሕአዴግ ዘመን፣ ሶስቱም ኢትዮጵያን በከፍተኛ ጀግንነት እና ብቃት ያገለገሉ ወታደሮች ናቸው። ቅድመ አያቶቼም በሁለቱም በኩል እነ ቀኛዝማች ደስታ ብሩ እና ብላታ ጥሩነህ ኪዳኑ እንደአብዛኛው የጎጃም፣ አማራ ገበሬ አርበኞችም ነበሩ። ቤተሰቤ ለሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት በደም ዋጋ የከፈለ ነው። ባንዳነት ከእኔም ሆነ ከቤተሰቤ ታሪክና እሴት ጋር ባዳ ነው። ስለዚህ ባንዳ ያላችሁኝ ተቺዎቼ ባንዳነት ይኖርባችሁ ከሆነ በዙሪያችሁ ፈልጉ፣ ከኛ ቤት ባንዳ የለም ነው መልሴ።
ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረብሁት ጥያቄ ዓላማው አጣዳፊ የውስጥ ችግሮችን ከማስቀደም ይልቅ የባሕር በር አጀንዳን በማስቀደም በውጭ ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረጉ ስልታዊ ስህተት መሆኑን ለማሳየት ነው። ስለዚህም የሀገሪቱ የፖለቲካ ጉልበት በመጀመሪያ የውስጥ ሰላም ግንባታ ላይ እንዲውል አሳስቤያለሁ።
ከዚህ በተረፈ እግዚአብሔር ይመስገንና በሙያዬ የትም ዓለም ሂጄ ሰርቼ ኑሮዬን ማሸነፍ የምችልበት የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ አለኝ። በፖሊሲ አውጪነት እና ከፍተኛ አመራርም በቂ ልምድ አለኝ። ስለዚህ ኑሮዬን ለመደጎም የየትኛውም አካል ቅጥረኛ የመሆን ግዴታ የለብኝም። ለጊዜው ግን እኔ የባሕር ዳር ሕዝብና የአማራ/የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካይ እንደራሴ ነኝ፤ የምወክለውም የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ብቻ ነው!
ክስ ሁለት፦ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷን ትቃወማለህ
በፓርላማው ንግግሬ “ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የሚደረግ ማንኛውንም አይነት ዲፕሎማሲያዊ ጥረትን የምቀበለው ነኝ” ብዬ በግልጽ አመላክቻለሁ። የባሕር በር ማግኘት ብሔራዊ ጥቅም መሆኑን እንኳን እኔ 8ኛ ክፍልን ያጠናቀቀ የአንድ መስሪያ ቤት ፖስተኛ እንኳን ይገነዘበዋል።
ተቃውሞዬ ያለው የባሕር በርን በተመለከተ በጉዳዩ አያያዝ ዘዴ ላይ ነው። መንግስት የባሕር በርን እንደ “ህልውና ጥያቄ” በማቅረብ ሀገሪቱን ወደ ጦርነት አፋፍ እየመራ መሆኑን ተችቻለሁ። የእኔ አቋም የባሕር በር ጥያቄው በሰላማዊ፣ በሕጋዊና ሰጥቶ መቀበልን መሠረት ባደረገ አካሄድ ብቻ መፈታት አለበት የሚል ነው። ሀገራችን አሁን በውስጥ ጦርነት ተወጥራ ባለችበት ሁኔታ፤ የውስጥ ዘላቂ ሠላምን ማረጋገጥ ሲገባት በባሕር በር ስም ተጨማሪ የውጪ ጦርነት ውስጥ በመግባት በዚህ ጉዳይ ሌላ የዜጎች ደም እና ሕይዎት መክፈል የለባትም ነው። ጦርነትን የሚጋብዝ አካሄድ መቃወም የሀገር ፍቅር እንጂ ባንዳነት አይደለም። በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ሕወኃት/የትግራይ ኃይሎች በወገኖቼ ላይ ማይካድራን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የፈጸሙትን የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር ማጥፋት እና ሁለንተናዊ የጦር ወንጀል በመቃወም አማራ ክልል ውስጥ የተደረገውን ራስን የመከላከል ጦርነት ደግፌያለሁ፣ ግን አልኩራራበትም (በአማራ ህዝብ ላይ የጦር ወንጀል የፈጸሙ የትግራይ ኃይሎች በፍትህ አደባባይ መቅረብ እንዳለባቸው በተደጋጋሚ እንደገለጽሁት ሁሉ፣ በትግራይ በንጹኃን ተጋሩዎች ላይ በተፈጸመው የጦር ወንጀል ውስጥ የተሳተፈ ማንኛውም አካልም በተመሳሳይ በፍርድ አደባባይ እንዲዳኝ እፈልጋለሁ)። ስለዚህ ራስን የመከላከል የግዴታ ጦርነት ካልሆነ፣ አባቱ የጦርነት ሰለባ የሆነ ወታደር ልጅ እንደመሆኔ ጦርነትን በየትኛውም ምክንያት አልደግፍም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ስላረበበው የጦርነት ስጋት ላቀረብሁት ጥያቄ በምላሻቸው የባህር በር ለማግኜት የግድ ጦርነት ውስጥ መግባት የለብንም የሚለውን ነገር አስረግጠው ተናግረዋል (ዛቻውን እንደ ባርጌይኒንግ ችፕና የዲፕሎማሲ ቀዳዳ መፍጠሪያ ጫና ማድረጊያ ታክቲክ አድርጌ ነው የተረዳሁት)።
ክስ ሦስት፦ ሁልጊዜ ትችት ብቻ እንጂ አማራጭ ሀሳብ የለህም
ይህ ሀሳብ አብዛኛውን ጊዜ የፖለቲካ ሀሁ ከማይረዱ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በተደጋጋሚ የሚነሳ ነው። አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ የሕዝብን ችግሮች እና እሮሮዎች እንዲሁም የመንግሥትን ክፍተት ማሳየት ዋናው ሥራው ቢሆንም፣ በጥያቄዎቼ እና በንግግሬ ግን ከመተቸት ያለፈ ግልጽ አማራጭ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን አቅርቤያለሁ።
ሀ) የጸጥታ ጉዳይን የተመለከተው አማራጭ፦ ለአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ከወታደራዊ አማራጭ ውጪ የተለየ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲፈለግ ጠይቄያለሁ። ከትግራይ ኃይሎች፣ ከፋኖ እና ከኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር መንግስት የገባበትን ሁኔታ በአርቆ አስተዋይነት በድርድር እንዲፈታ ግልጽ ጥሪ አቅርቤያለሁ።
ለ) የኢኮኖሚ ጉዳይን የተመለከተው አማራጭ፦ የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር መንግሥት አዲስና አስቸኳይ ዕቅድ እንዲያቀርብ እንዲሁም ወሳኝ ማኅበራዊ ወጪዎችን ሳይቀንስ የውጭ ዕዳውን ለመክፈል ሚዛናዊ የፊስካል ፖሊሲ እንዲከተል ግፊት አድርጌያለሁ።
ሐ) የውጭ ግንኙነት ጉዳይን የተመለከተው አማራጭ፦ የመንግሥት ከፍተኛ የፖለቲካ አቅም የውስጥ የፖለቲካ ግጭቶችን ለመፍታትና ከዜጎች ጋር ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር እንዲውል በግልጽ ጠቁሜያለሁ። የኢህአዴግ የውጪ ፖሊሲ ጠንካራ ጎን የነበረው መርሆ “የውስጥ ሰላም የውጭ ስኬት መሰረት ነው!” የሚለውን እኔም የምገዛው የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ መርህ ነው።
እንደ ማጠቃለያ፦ በገዢው ፓርቲ ላይ በማንኛውም ጊዜ የማቀርበው ትችቴ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ቆሜ የምጠይቀው ሕጋዊ የፖለቲካ ትችት እንጂ በቅጥረኝነት የመጣ አይደለም። የገዢው ፓርቲ ኃላፊነት የፖለቲካ ትችትን በአላዋቂዎች የብሔራዊ ክህደት ክስ ለማኮላሸት ከመሞከር ይልቅ ለቀረቡት ወሳኝ ጥያቄዎች አሳማኝና ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ነው።
የእኔ የፖለቲካ ሥራ ትኩረት ደግሞ በተረዳሁት ልክ የሕዝቤን ህልውና እና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ማስከበር ነው!
(ፎቶ፦ የተቃዋሚ የፓርላማ አባላት የሆኑ ወዳጆቼ አቶ ባርጠማ እና አቶ ብርሐኑ ጋር ፤ በምክር ቤቱ ጥያቄ ባቀረብሁበት ወቅት የተወሰደ።)( ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ )
