የኤርትራ ፕሬዝደንት ግብፅን ለመጎብኘት ወደ ካይሮ ተጓዙ

የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ግብፅን ለ5 ቀናት ለመጎብኘት ዛሬ ከአስመራ ወደ ካይሮ ተጉዘዋል። የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል በX ገፃቸዉ ዛሬ (ሐሙስ ጥቅምት 20 ቀን፣ 2018 ዓ.ም) እንደዘገቡት ፕሬዝደንት ኢሳያስ ግብፅን የሚጎበኙት የግብፅ ፕሬዝደንት አብዱልፈታሕ አል ሲሲ ባደረጉላቸዉ ግብዣ ነዉ። ሁለቱ መሪዎች የሁለቱን ሐገራት ግንኙነት ይበልጥ «ለማጠናከርና ለሁለቱ ሐገራት በሚጠቅሙ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች» ላይ ይወያያሉ ተብሏል። ፕሬዝደንት ኢሳያስ በቅርቡ የተገነባዉ የግብፅ ታላቅ ቤተ-መዘክር (ሙዚየም) በመጪዉ ቅዳሜ በሚመረቅበት ድግስ ላይም ይገኛሉ ተብሏል። የሁለቱ ሐገራት መሪዎች «በጋራና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ» ይነጋገራሉ የተባለዉ ሁለቱም መንግሥታት ይሳተፉበታል የሚባለዉ የሱዳን ጦርነት በናረበት ወቅት መሆኑ ነዉ። በግብፅ፣ በኤርትራና በሌሎችም የአካባቢዉ ሐገራት ይደገፋል የሚባለዉ የሱዳን መከላከያ ኃይል፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ይደገፋል በሚባለዉ በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር (RSF) ጠላቱ ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ዳርፉር ዉስጥ ሽንፈት ገጥሞታል።
ከዚህም በተጨማሪ የፕሬዚደንቱ ጉብኝት ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ሰበብ ከግብፅ፣ በወደብ ጉዳይ ደግሞ ከኤርትራ ጋር የገጠመችዉ እሰጥ አገባ ባየለበት ወቅትም ነዉ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈዉ ማክሰኞ ከሐገሪቱ ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት መልስና ማብራሪያ ለኢትዮጵያ “የቀይ ባሕር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው” ብለዋል።
ባለፈዉ መጋቢት የግብፅ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በድር አብድላትይ ከፕሬዝደንት አብዱልፈታሕ አል ሲሲ የተላከ መልዕክት ለፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈርቂ ለማድረስ በሚል አስመራን ጎብኝተዉ ነበር። ጉብኝቱና መልዕክቱ በግብፅ፣ በኤርትራና በሶማሊያ መካከል «የአካባቢዉን ሠላም የማጠናከር የትብብር ሥልት» በተባለዉ የሦስትዮሽ ወዳጅነት ላይ ያተኮረ ነዉ ተብሎም ነበር።