መሠረት ሚድያ)- በአርሲ ሀገረ ስብከት ውስጥ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ብቻ በታጣቂዎች በተፈፀሙ ሶስት የተለያዩ ጥቃቶች 22 ሰዎች መገደላቸው ታውቋል።
ማኀበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎት ዛሬ እንደዘገበው በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በሆንቆሌ ዋቤ ወረዳ በቀቅሳ ቀበሌ ትናንት ጥቅምት 18 ለ19 አጥቢያ ከምሽቱ 4፡00 ላይ አምስት ምእመናን በታጣቂዎች መገደላቸው በአካባቢው ያሉ ምእመናንን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሁለት ወንድማማቾች እና ሁለት እህትማማቾች የሚገኙ ሲሆን በተጨማሪም አንድ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታይ ከቤተሰቡ አባላት ጋር መገደሉ ታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ በወረዳው በሚገኘው በቀቅሳ ቀበሌ የእግዚአብሄር አብ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ታግተው መወሰዳቸው ታውቋል። በአካባቢው የሚኖሩ ምዕመናን በአሁኑ ሰዓት የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ ይገኛሉ።

በተመሳሳይ ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ከለሊቱ 4 ሰዓት አካባቢ በምሥራቅ አርሲ ሽርካ ወረዳ ሄላ ዘባባ ቀበሌ አርሴማ አጥቢያ የሚኖሩ ምእመናን በታጠቁ ኃይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሦስቱ መገደላቸው እና አራቱ ደግሞ መታገታቸው ተገልጿል።
ከተገደሉት ምእመናን ውስጥ የአንዱ ሟች አባትና ወንድም መታገታቸው በመረጃው የተገለጸ ሲሆን ታፍነው የተወሰዱት ምእመናን ስለሚገኙበት ሁኔታ አይታወቅም ተብሏል፡፡
በመረጃው እንደተነገረው የሞቱት ሦስቱ ግለሰቦች ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
በሶስተኛነት በአርሲ ሀገረ ስብከት ጉና ወረዳ በሚገኘ ኖኖ ጃዊ ቀበሌ የሚኖሩ 14 ምዕመናን ከለሊቱ 6 ሰዓት አካባቢ በዕለተ ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ለ14 አጥቢያ ከተኙበት ከቤታቸው አስወጥተው የታጠቁ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሲሆን ስድስቱ ከመገደላቸው ከአንድ ቀን በፈት ቀድመው ታፍነው ተወስደው ነበር ተብሏል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ማለትም ከ2016 ዓ.ም መስከረም 02 ጀምሮ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ያለማቋረጥ በወረዳው ከ115 በላይ ምእመናን የተገደሉ ሲሆን 27 ምዕመናን ደግሞ አሁንም ድረስ ታግተው ያሉበት እንደማይታወቅ ነዋሪዎቹ ለብሮድካስት አገልግሎቱ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በወረዳው ካሉ 37 አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከ16 በላይ የሆኑት አገልግሎት የማይሰጡ መሆናቸውንና ከእነዚህም መካከል 3ቱ ሙሉ በሙሉ መዘረፋቸውን ተጠቅሷል።
ነዋሪዎቹ እየደረሰ ያለው የሰው ሕይወት እልፈት፣ መታገትና የንብረት ውድመት ችግር እልባት አንዲያገኝ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን እና የመንግሥት ባለድርሻ አካላት አሁንም ትኩረት ሰጥተው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
-መሠረት ሚድያ-