“እንደ ሀገር ስንት ትውልድ በጦርነት እየበላን እንቀጥላለን” ሲሉ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠየቁ!
ዶክተር ደሳለኝ “10 ድስት ጥዶ አንዱንም ሳያማስል ሁሉንም የማሳረር ተግባር እየፈፀመ ነው” ሲሉም አገዛዙ የውስጥ ችግሩን ሳይፈታ ቀይ ባህርና መሰል የማጭበርበሪያ አጀንዳ መምዘዙን በፅኑ ተችተዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምፅ ይሆኑኛል ብሎ የመረጣቸው የፓርላማ አባላት፡ ለመረጣቸው ሕዝብ ሳይሆን ነውረኛው ዐብይ አህመድ ያስቀመጣቸው ካድሬዎች እስኪመስሉ ድረስ “ዐብይ ሺ ከመት ንገስ” የሚል ይዘት ያለው የመወድስ አይነት ሲያቀርቡ በዋለበት በዚህ የፓርላማ ውሎ፡ መራር የሆኑ እውነታዎችን ያዘሉ ጥያቄዎች ደግሞ በዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ መነሳታቸውን መረብ ሚዲያ ተመልክቷል።
እነዚህ ጥያቄዎች ምንም እንኳን መላሽና ምላሽ ባይኖራቸውም ነገር ግን ዶ/ሩ የጠየቁት ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው።
1ኛ፦ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ የህዝቡን ጥያቄ ማቅረብ ተስፈኛነት እንጂ ጨለምተኛነት አይደለም ያለው ዶክተሩ፡ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሱ ግጭቶች ተባብሰው ቀጥለዋል፡፡ በእነዚህ ግጭቶች የተጎዱ ንጹሀን ነዋሪዎች እና የንጹሀን መሰረተ_ልማት ጉዳቶች ቁጥር በግልጽ ሊነግሩን ይችላሉ ወይ ?
2፦ መንግስት ችግሮችን ለመፍታት ጽንፈኛ እና አሸባሪ የሚሏቸውን ቡድኖች ከመውጋት ባለፈ ለሁለቱ ክልሎች ከወታደራዊ አማራጮች ውጪ ያሉ ፖለቲካዊ መፍትሄዎችን ለመስጠት ለምን አይሰራም?
3ኛ፦ የኢትዮጵያ ህዝብ ተንቀሳቅሶ በሰላም ሰርቶ መኖር አቅቶታል፡፡ የሰላም እጦት ሰልችቶታል፡፡ሀገራችን እንደ ኮሎምብያ ከውስጥ ታጣቂዎች ጋር ለ 50 አመታት ስትዋጋ አትኖርም፡፡ በህግ ማስከበር ስም የሚወሰድ የዘፈቀደ እስር ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ የፖለቲካ እና የህሌና እስረኞች ጉዳይ እልባት እንዲሰጠው ብንጠይቅም ምላሽ እየተሰጠ አይደለም ያሉት ዶ/ር ደሳለኝ፡ በዚህ ሁኔታ ቀጣዩ ምርጫ ነጻ እና ፍትሀዊ እንደሚሆን ምን አይነት ዋስትና ይኖራል?
4ኛ፦ መንግስት ዋና ትኩረቱን በአፋጣኝ እልባት ከሚፈልጉ በሀገር ውስጥ ያሉ የጸጥታ ችግሮች ላይ ከማዋል ይልቅ ወደ ሀገር ውጪ እና ወደ ቀይ ባህር አዙሯል፡፡ መንግስት ዋና ትኩረቱን ለምን ከራሱ ህዝብ እና ከራሱ ሀገር ችግር ጋር አያደርግም ?
5ኛ፦ መንግስት አሥር ድስት ጥዶ አንዱንም ሳያማስል እንደ ማሳረር ነው፡፡ መንግስት አንዴ ከኤርትራ ጋር፤ አንዴ ከሶማሊያ ጋር፤ ሌላ ግዜ ከጁቡቲ ጋር የሚደረግ ሙከራ ነገር ግን ፍሬ የማያፈራ መፍጨርጨሮች ይታያሉ፡፡ መንግስት ከትግራይ ሀይሎች ጋር ከፍተኛ መካረር ውስጥ ገብቷል፡፡ እንደ ሀገር ስንት ትውልድ እየበላን እንቀጥላለን? ካለፈው ስህተታችን የምንማረው መቼ ነው? መንግስት ከእነዚህ ታጣቂ ሀይሎች ጋር በሰላማዊ እና በድርድር ችግሮችን እንዲፈታ፡ ከቀይ ባህር ጋር የገባበትን ውጥረትም በህጋዊ እና ሰጥቶ መቀበል መርህ እንዲያስተካክል ለምን አይደረግም? ሲሉ ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ለጥያቄዎቹ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በመደናገጥ የታጀበ ፌዝ የተሞላበት ንግግር ሲያደርጉ ተደምጠዋል።