” የኑሮ ሁኔታ በጣም ከባድ ነው የሚከፈለን ብር 760 ነው፡፡ … እኛ ሴቶች እንጨት ለቅመን ነው የምንማረው ወንዶችም እንጨት እየለቀሙ እየጋገሩ ይማራሉ ” – የመምህራን ማሰልጠኛ ተማሪዎች
ከ40 አመት በላይ መምህራንን በማሰልጠን የሚታወቀዉ የደሴ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ በመምህርነት በዲግሪና ዲፕሎማ የሚሰለጥኑ ተማሪዎች በወር ለምግብ የሚሰጣቸዉ 760 ብር ለመኖር ስላላስቻላቸዉ ሰዉ ቤት ተቀጥረዉ በቤት ሰራተኝነት ከጫካ ጭራሮ እየለቀሙ የራሳቸውን ምግብ ለማብሰል መገደዳቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ ተማሪዎች አንዱ በእንጨት ለቀማ ወቅት ሕይወቱ እንዳለፈም ሰልጣኞቹ ተናግረዋል።
በወር የሚከፈላቸው 760 ብር ነው ፤ አንድ እንጀራ ለመግዛት የዋጋውን ውድነት አልቻሉትም ከዚህ ኑሮ ውድነት በመነሳት ወንዶች ኩሽና ተፈቅዶላቸው እንጀራ እየጋገሩ እየኖሩ ናቸው።
ነገ ተማሪዎችን ለማስተማር የሚሰለጥኑ መምህራን የሚማሩትን ሳይሆን የሚበሉትን በማሰብ የማገዶ እንጨት በመልቀም፣ የቀን የጉልበት ሠራተኛ በመሆን፣ እንዲሁም ሊጥ አብኩተው ለምግባቸው የሚሆን እንጀራ በመጋገር ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ ነው የተባለው።
ሰልጣኝ መምህራኑ ለዶቼ ቨለ ሬድዮ ምን አሉ ?
በ760 ብር የምግብ ወርሃዊ ክፍያ የመኖሪያ ቤት ተሰጥቷቸው በኮሌጅ የሚማሩ ተማሪዎች ከትምህርት በኋላ የሚመገቡትን ምግብ ለማብሰል በደሴ ወደሚገኙት የጦሳ፣ አዘዋና ሌሎች እንጨት ለመልቀም ወደሚያስችላቸው ጫካዎች ሲያመሩ ከሞት ጋርም ተጋፍጠዋል፡፡
ለመማር በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ በጦሳ ተራራ እንደዚሁም በአዘዋ ተራራ ካለቀምን በስተቀር እንጨት አይገኝም ብለዋል።
በዚህም አንድ ሳሙኤል የተባለ የእንግሊዝኛ ክፍል የዲግሪ ተማሪ በጦሳ ተራራ እንጨት ሊለቅም ሄዶ ህዳር 28 ቀን ህይወቱ አልፏል፡፡
ችግሩ በተለይ ሴቶች ላይ የጎላ ነው የምትለው ሠልጣኝ ተማሪ የግማሽ ቀን የቤት ሰራተኝነትና በሌሎች ስራዎች እራሳችን እየደጎምን ነው ትምህርት የምንማረው ብላለች፡፡
” የኑሮ ሁኔታ በጣም ከባድ ነው የሚከፈለን ብር 760 ነው፡፡ ባለን አቅም እየሰራንም ነው የምንማረው በትምህርታችን ላይ ውጭ ውለን ስንገባ እየደከመን ማጥናት እንቸገራለን እንጨት ለቅመን ነው የምንማረው ወንዶችም እንጨት እየለቀሙ እየጋገሩ ይማራሉ ” ስትል ተናግራለች።
” አሁን አሁንማ ሥራም ጠፍቷል ፤
አሁን የቀን ስራ ሰርተን ለመማር የማንችልበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ” የሚለው ተማሪ ” ወቅታዊ ሁኔታው ተጨማሪ ስራ ሰርተን ለመማር አላስቻለንም ” ብሏል።
” ሴቶች የግማሽ ቀን ስራ ካገኙ ይሰራሉ ወንዶች ቅዳሜና እሁድ ይሰራሉ። ዘንድሮ ግን የለም፤ መስራት አትችልም የተግባር ልምምድ ስለምንሄድ ትንሽ ከበድ ይላል። ባለፈው አመት ይሻላል ውጭ ላይም ትንሽ አስፈሪ ነው ሰዓቱ ” ሲል ገልጿል።
በትምህርቱ ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው መባሉን
የደሴ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ መምህር የሆኑት መምህር አበበ ደሴ እንደሚገልፁት ተማሪዎች የዕለት ኑሯቸውን በማሰብ ስለሚጠመዱ ትምህርት የመቀበል አቅማቸው ውስን ሆኗል ብለዋል፡፡
” ግማሾች የቀን ስራ ሰርተው ነው የሚኖሩት። ሴቶችም ቢሆኑ በእንጀራ ጋጋሪና ካፍቴሪያ ውስጥ ተቀጥረው እየሰሩ ነው። ክፍል ውስጥም ገብተው ስታይ በአብዛኛዉ ከሚማሩበት የሚያንቀላፉበት ነው የሚበልጠው። ወጥተው የሚመገቡት የለም ” ሲሉ አስረድተዋል።
የደሴ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሀሰን ወርቁ በበኩላቸው ተማሪዎቹ ያሉበት ችግር ለመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ እንቅፋት ፈጥሯል ብለዋል።
ወርሃዊ የምግብ ክፍያቸውም ከ760 ብር ከፍ እንዲል ለክልሉ ትምህርት ቢሮ/ጥያቄ መቅረቡን አመልክተዋል።
” በአብዛኛው ከመማር ማስተማሩ ይልቅ ስለ እሚበሉት ፣የሚጠጡት ነው የሚያስቡት በትምህርት ላይ ተፅዕኖ አለው። ይህንን ታሳቢ አድርገን ክልል ላይም ጥያቄ እያቀረብን ነው፡፡ ” ብለዋል።
Credit – ዶቼ ቨለ ሬድዮ