እናት ፓርቲ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጣሪያና ግድግዳ ግብር መመሪያ ተግባራዊ እንዳይኾን የጣለውን እገዳ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሠሚ ችሎት ትናንት እንደሻረው አስታውቋል። ይግባኝ ሠሚ ችሎቱ፣ ከሳሽ ተከራይ እንጂ ቤትም ኾነ ቦታ እንደሌለው፤ በጉዳዩ ላይ መብትም ኾነ ጥቅም እንዲኹም በፍርድ ቤት እንዲከራከር የወከለው አካል እንደሌለ ገልጦ፣ የሥር ፍርድ ቤት ኹለቱን ወገኖች ማከራከር አልነበረበትም በማለት መወሰኑን ፓርቲው ገልጧል። እናት ፓርቲ በ2015 ዓ፣ም የወጣው መመሪያ ሕገወጥ መኾኑን ጠቅሶ በአስተዳደሩ ላይ በመሠረተው ክስ መሠረት፣ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መመሪያው ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም በማለት በጥር 2017 ዓ፣ም መወሠኑ ይታወሳል።