የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር በዓመት ውስጥ እስከ 15 ሺሕ ጨምሯል።

የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር በዓመት ውስጥ እስከ 15 ሺሕ ጨምሯል።

አማኑኤል የአዕምሮ ህሙማን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሆስፒታሉ የሚስተናገዱ የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር በዓመት ውስጥ እስከ 15 ሺሕ መጨመሩን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጸ፡፡

ይህን ያሉን፣ የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር እየጨመረ ወይስ እየቀነሰ ነው ? ግጭትና ጦርነት የህሙማኑን ቁጥር ለመጨመር ገፊ መንስኤ አልሆነም ? ስንል የጠየቅናቸው የአዕምሮ ሐኪምና የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ክብሮም ኃይሌ ናቸው።

ዳይሬክተሩ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በዝርዝር ምን አሉ ?

” የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ግጭት፣ ድርቅ፣ ጦርነትና መፈናቀሎች በተደጋጋሚ አጋጥመዋል። እነዚህ ክስተቶች የአዕምሮ ጤና ችግርን እንደሚጨምሩ የሚያሻማ አይደለም።

ካለፈው ዓመት መጠነኛ ጭማሪ አለው፡፡ የ2017 እስከ ሰኔ ያለው ከ130 ሺሕ ትንሽ ከፍ ይላል፤ በዚያኛው ዓመት ካየነው 10 ሺሕ፣ 15 ሺሕ ጭማሪ አለው።

ስለዚህ የመጨመር ሁኔታዎች አሉ፤ እንደሚጨምርም ይታወቃል፡፡ ግን ሁሉም (ታማሚ) አይመጣም፡፡ ስለዚህ የሆስፒታሉ ዳታ ማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ላያሳይ ይችላል። ስለዚህ እኛ ጋር ያለው የታካሚ ቁጥር መጨመር አለመጨመሩ የችግሩን መኖር አለመኖሩን (ሙሉ በሙሉ) አያሳይም።

የአማኑኤል ሆስፒታል የህሙማን ፍሰትን የሚያግዱ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ለአብነትም በገንዘብ አቅም ማነስ፣ በሚያግዝ ሰው አለመኖር ህሙማን ላይመጡ ይችላሉ።

የመፍትሄ ሀሳብ ምን ሰጡ ?

” እኛ ነን ችግሩ ወዳጋጠመበት ቦታ መሄድ ያለብን፡፡ በአንድ ቦታ ግጭት ሲያጋጥም ‘ወገኖቼ ይሞታሉ’ በሚል መሸበር ይኖራል፡፡ በተለይ በዚያ ወቅት ስነ ልቦናዊ ድጋፍ ካልተገኘ ችግሩ ይብሳል።

ስለዚህ አዕምሮ ጤናም ጉዳይ ሌሎች እርዳታዎች ጋር አብሮ መሄድ አለበት፡፡ በግንዛቤ እጥረት በትራንስፖርትና በሌሎች ምክንያቶች ሰዎች ወደ ህክምና ላይመጡ ይችላሉ፡፡ ስነልቦናዊና ማኀበራዊ ድጋፉን በዚያው ማቅረብ ያስፈልጋል፣ የታመሙ ከሆኑም እኛ መሄድ አለብን።

በሌላ በኩል፣ ሰዎች ድባቴ ውስጥ በሚገቡበት ወቅት ከሚያወቋቸው ሰዎች ጋር ጊዜ ቢያሳልፉ፣ ችግራቸውን ቢወያዩ ለአዕምሮ ህመም የመጋለጥ ሁኔታው ይቀንሳል።

የሆስፒታሉ ተመላላሽ ህክምና ክፍል ኃላፊስ ምን አሉ ?

የሆስፒታሉ የተመላላሽ ህክምና ክፍል ኃላፊ ሳሙኤል ቶለሳ፣ የዘንድሮው የአዕምሮ ጤና ቀን ” በድንገተኛ አደጋዎችና ሰብዓዊ ቀውስ ወቅት የአዕምሮ ጤና አገልግሎት ተደራሽነት ምን ይመስላል ? ” የሚለው ላይ እንዳተኮረ ገልጸዋል።

” ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእርስበርስ ግጭቶች አሉ፣ ያን ተከትሎ የሚመጡ ማኅበራዊ ቀውሶች አሉ ” ያሉት ኃላፊው፣ በዚህም የተደራሽነት ውስነት መኖሩን ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

” በተለያዩ ክልሎች ያለው ቀውስ ራሱን የቻለ ተፅዕኖ አለው፣ ተማሪዎች እንዳይማሩ የማድረግ ሂደቶች አሉ ” ብለው፣ ሰዎች ቀጥተኛ የጦርነቱ ተጠቂ ሲሆኑና የሚያስጨንቁ ነገሮች ሲፈጠሩ ለአዕምሮ ህመም ተጋላጭነታቸው እያደገ እንደሚመጣ ገልጸዋል።