በሽብር የተከሰሱ እስረኞቹን ለይተው ከጠበቆቻቸው ጋር እንዳይገናኙ በሚል በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ተከልክለናል

በአማራ ክልል ካለው የፀጥታ መደፍረስ ጋር በተገናኘ የፋኖ ታጣቂዎችን ትደግፋላችሁ በሚል በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙ እስረኞች ከጠበቆቻቸው ጋር እንዳይገናኙ መከልከላቸውን ቤተሰቦቻቸው ለመሠረት ሚዲያ ተናግረዋል።
“እስረኞቹ ከጠበቃቸው ጋር እንዳይገናኙ ተከለከሉ የተባለው ምን ያህል እውነት ነው?” ስንል ከጠበቆቹ አንዱ የሆኑትን አቶ ሰለሞን ገዛኽኝን ጠይቀናቸው ነበር።
አቶ ሰለሞን ጉዳዩ እውነት መሆኑን አረጋግጠው “እስረኞቹን አግኝተህ የሕግ አገልግሎት መስጠት አትችልም በሚል የተከለከልኩት እኔ ነኝ” ሲሉ ገልፀዋል።
“ከእስረኞቹ ጋር እንዳይገናኙ የተከለከሉበት ምክንያት ምንድን ነው?” ተብለው ከመሠረት ሚዲያ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ደግሞ “ካሳለፍነው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ ጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም ድረስ በሽብር የተከሰሱ እስረኞቹን ለይተው ከጠበቆቻቸው ጋር እንዳይገናኙ በሚል በማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ተከልክለናል” ሲሉ አቶ ሰለሞን አክለዋል።
ጠበቃው ጨምረውም “እንኳን ጠበቆቻቸው ቤተሰቦቻቸው ገብተው እንዳይጠይቋቸው ከፍተኛ ጫና እየተደረገባቸው ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በሽብር ወንጀል የተከሰሱ እስረኞቹ ከሌላው በተለየ ሁኔታ ሕክምና ሳይቀር እየተከለከሉ ነው ያሉት ጠበቃ ሰለሞን በጠና ታመው አልጋ ላይ የዋሉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ዶክተር ካሳ ተሻገር ሕክምና እንዳያገኙ ከተከለከሉት እስረኞች ውስጥ አንዱ ናቸው ብለዋል።
ዶክተር ካሳ በጀርባ ዲስክ መንሸራተት ምክንያት መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ የተናገሩት ጠበቃው ማረሚያ ቤቱ ለማሳከም ፍቃደኛ አልሆነም ብለዋል።
ይህንን በእስረኞቹ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ጫና አስመልክቶ አቤቱታ ለማቅረብ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የጥበቃ እና ደኅንነት ማስተባበሪያ ኃላፊ ኢንስፔክተር ድሪባ ሰንበታን የጠየቁት አቶ ሰለሞን ተቋሙን የማይወክል እና ራሳቸውን የሥርዓቱ ተወካይ አድርገው በመቁጠር የማይገባ መልስ ሰጥተውኛል ብለዋል።
የእስረኞችን አቤቱታ እና የማረሚያ ቤቱን ያልተገባ መልስ በማጣቀስ በቀጣይ ሳምንት ፍርድ ቤት እንደሚከሱ የነገሩን አቶ ሰለሞን በዛሬው ዕለት በዚሁ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ መሪጌታ በላይ አዳሙ የተባሉ ደንበኛቸው በጥበቃ ፖሊሶች መደብደባቸውን እና በአሁኑ ወቅትም ሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛል ሲሉ ገልፀዋል።
መሪጌታ በላይ በአማራ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የትጥቅ ትግል ትደግፋላችሁ በሚል ከታሰሩ ሦስት መቶ ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ ናቸው።
ምንጭ – መሠረት ሚድያ