የዩናይድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ፣ ኢትዮጵያ ለዉጪ የኢንቨስትመንት ፈታኝ ሐገር ናት » አለ
የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ሰሞኑን ባወጣዉ መረጃ “የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኹኔታ “ለአሜሪካ እና ለሌሎች የውጭ ኩባንዮች ፈታኝ ነው” ሲል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የከተሞች የመንገድና የወንዝ የዳርቻ ወይም የኮሪደር ልማት የባለሃብቶችን መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ የማድረግ ፍላጎት “ገድቧል” ሲል ነው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በሪፖርቱ ያመለከተው። ዘገባዉ “የውጭ ይዞታዎችን ጨምሮ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እና የንግድ ድርጅቶች ንብረታቸው ያለ በቂ ማስጠንቀቂ መፍረሱን ተከትሎ እዚህ ድምዳሜ ላይ መድረሱን ይጠቅሳል።
ግጭት በሚካሄድባቸው አማራና ኦሮሚያ ክልሎች የመንቀሳቀስ ሁኔታ ገደብ መኖሩን የጠቀሰው ይህ ሪፖርት ባለሥልጣናት ወይም ታጣቂ ቡድኖች በተደጋጋሚ የግል ንብረቶችን እንደሚነጥቁ፣ የንብረት ባለቤትነት መብቶች በቂ ጥበቃ እያገኙ እንዳልሆነ ጭምር አመልካቾችን ጠቅሷል።
የፖለቲካ ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን በሰጡት አስተያየት፤ «የመጀመርያው የሰላም ጠቋሚ – ሰላምና ፀጥታ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ግልጽነት እና ተጠያቂነት። ለምሳሌ አንድ ምርት ወይም አገልግሎት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሲንቀሳቀስ ምን ያህል ዋስትና አለው? የሚለው ነገር ይታያል። ዋስትና ብቻም ሳይሆን ለዚያ ለንብረትህ ሕጋዊ ጥበቃ የሚያደርግ የመንግሥት የአሠራር ሥርዓት ጥብቀቱ ምን ያህል ነው? የሚለውም ይጠናል።» ማለታቸውን የአዲስ አበባው ወኪላችን ሰሎሞን ሙጬ ዘግቧል።