በተመድ ዓመታዊ የፈጠራ ሪፖርት ኢትዮጵያ ከ139 አገሮች 134ኛ ደረጃ ተሰጣት – ሪፖርተር
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አዕምሯዊ ንብረት መብቶች ድርጅት እ.ኤ.አ. የ2025 ዓመታዊ የፈጠራ ብቃት ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን ከዓለም 139 አገሮች 134ኛ፣ ከአፍሪካ ደግሞ 28ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አስታወቀ፡፡
የአገሪቱን የፈጠራ ቁመና ለመለካት ከ80 በላይ አመላካች መሥፈርቶችን መጠቀሙን በማስታወቅ የጥናትና ምርምር፣ የካፒታል ፍሰት፣ ከፍተኛ ቴክኖሎጂዎችን ለውጭ አገር ገበያ የማቅረብ አቅም፣ የአዕምሯዊ ንብረት አያያዝና በርካታ ጉዳዮችን በመዳሰስ ባለ 300 ገጽ ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡
ዓመታዊ ሪፖርቱ ሌሴቶን በ132ኛ፣ ጊኒን በ23ኛ፣ ኢትዮጵያን በ134ኛ፣ ማሊን በ35ኛ፣ ቬኑዘዌላን በ136ኛ፣ ኮንጎን በ137ኛ፣ አንጎላን በ38ኛ እና ኒጀርን በ39ኛ ደረጃ መድቧቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2024 130ኛ ደረጃ ይዛ የነበረ ሲሆን፣ በዚህኛው ዓመት ደረጃዋ ማሽቆልቆሉን ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡ ይሁን አንጂ በኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን ከኢንቨስትመንት ጋር በማስተሳሰርና የተሻለ ምኅዳር በመፍጠር ረገድ መሻሻል መኖሩን ያስረዳል፡፡
ዓመታዊ ጥናቱ እንደሚያሳየው አጠቃላይ የፈጠራ ደረጃዋ 134ኛ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ በተቋማት ብቃት 122ኛ፣ በሰው ሀብትና ጥናትና ምርምር 139ኛ፣ በመሠረተ ልማት 130ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ይላል፡፡ በተሰባጠረ የቴክኖሎጂ ገበያ 133ኛ፣ በቢዝነስ ምኅዳር 134ኛ፣ በዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር 82ኛ፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራዎች 139ኛ ላይ መድቧታል፡፡
ዓመታዊ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ኬንያና ሩዋንዳ ያነሰ አፈጻጸም ብታሳይም፣ በኦንላይን የመንግሥት አገልግሎት መልካም ጅማሮ፣ የብሮድባንድ የሞባይል ኢንተርኔት ተደራሽነትና ዲጂታል ምኅዳሮች ላይ መሻሻል እያሳች ያለች አገር መሆኗን አስረድቷል፡፡
ኢትዮጵያ በፈጠራ የተሻሉ የወደፊት ዕድሎች እንዳሏት ቢያሳይም፣ አሁንም የቀጠሉ መሰናክሎቿ፣ በተለይም የግሉ ዘርፍ በኢመደበኛ ኢንተርፕራይዞች የተያዘ መሆን፣ ለፈጠራ ሥራዎች ፋይናንስ የሚያቀርቡ አካላት አለመኖር፣ የትምህርት ዘርፍና የኢንዱስትሪው ደካማ የሆነ ቅርርብ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ቴክኖሎጂ የፈጠራ ቁመና ግርጌ ላይ አስቀምጧታል ይላል ሪፖርቱ፡፡
ኢትዮጵያ ከ139 አገሮች ጠርዝ ላይ ብትቀመጥም መንግሥት ይፋ ያደረገው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንና ኢትዮጵያን ለማዘመን የሚደረገው ጥረት፣ አዳዲስ ስታርትአፕ ቢዝነሶችን ለመደገፍ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና በቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋማት የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች መልካም ጅማሮች ናቸው ብሏል፡፡
ሪፖርቱ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድን፣ አሜሪካ፣ ኮሪያና ሲንጋፖር የዓለም የቴክኖሎጂ ቁንጮ ፈጣሪዎች ብሏቸዋል፡፡ ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ሞሪሺየስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናሚቢያ፣ ናይጄሪያና ሩዋንዳ የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ አገሮች መሆናቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ላይ በምታደርገው ጥናትና ምርምር በአገር አቀፍ ደረጃ በጣም ውስን ተቋማት ብቻ በዘርፉ ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ ደካማ መሠረተ ልማት፣ የኃይልና የኢንተርኔት መቆራረጥ፣ እንዲሁም የትራንስፖርት ዘርፍ አስተማማኝ አለመሆን፣ ለፈጠራ ሥራ ቁልፍ የሆኑና ነገር ግን በኢትዮጵያ አስተማማኝ ያልሆኑ አቅርቦቶች ሲል ሪፖርቱ አስቀምጧቸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ሰፊ የወጣት ኃይል ያለባት አገር ብትሆንም፣ የትምህርት ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ የሠለጠነ የሰው ኃይልን ማብቃት ላይ ሰፊ ክፍተት ያለበት መሆኑን የተመድ ሪፖርት ያስረዳል፡፡ From The Reporter Magazine