በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ሰዎች

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ሰዎች የቪዛ ጊዜያቸው ሲያልፍ የሚጣልባቸውን ቅጣት ለመክፈል ኢምባሲው ከእንግዲህ ብድር ለመስጠት ፍቃድ እንደሌለው አስታውቀዋል። ማሲንጋ አሜሪካዊያን ቪዛቸው ከማብቃቱ በፊት ከኢሚግሬሽን የቪዛ ማራዘሚያ ወይም የመኖሪያ ፍቃድ እንዲጠይቁ አሳስበዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አሜሪካዊያን የአገሪቱን የኢሚግሬሽን ደንቦች እንዲያከብሩና ቪዛቸው ወይም የመኖሪያ ፍቃዳቸው ጊዜ ከማለፉ በፊት እንዲያሳድሱም ማሲንጋ መክረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የቪዛ ጊዜ አሳልፎ መቆየትንና ሕገወጥ ስደትን ለመቀነስ ሲል የቪዛ ጊዜ አሳልፈው የሚቆዩ የውጭ ዜጎች ላይ የሚጣለውን ቅጣት ባንድ ቀን ወደ 30 የአሜሪካ ዶላር ማሳደጉን በኅዳር ወር ማሳወቁ ይታወሳል። መንግሥት አሜሪካዊያን እዳቸውን በሙሉ በዶላር እስኪከፍሉ ከአገር እንዳይወጡ መከልከል እንደሚችል መታወቅ አለበት ብለዋል።