ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤዶንጎሮ ወረዳ የታጠቂዎች እንቅስቃሴ እና ጥቃት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መጨመሩን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቋል፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች ላይ የነበረው የታጣቂዎች ጥቃት ወደ ከተማ ተዛምተው ትናንት ምሽት ወደ ወረዳው ዋና ከተማ ታጣቂዎች መግባታቸውንና በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደጫካ ሸሽተው እንደነበር ተገለፀ፡፡
DW Amharic ፡ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤዶንጎሮ ወረዳ የታጠቂዎች ጥቃት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቋል፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች ላይ ይስተዋል የነበረዉ የታጣቂዎች ጥቃት ወደ ከተማ ተዛምቶ ትናንት ምሽት ወደ ወረዳው ዋና ከተማ ታጣቂዎች መግባታቸው እና በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደጫካ ሸሽተው እንደነበር ዶቼ ቬሌ ያነጋገራቸዉ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ ከባለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ በወረዳው የሚስተዋለው የታጣቂዎች ጥቃት የነዋሪውን የዕለት ተዕለት እንቅስቅስቃሴ እያወከ ነዉ፡፡ የወረዳው አስተዳደር በበኩሉ ትናንት ምሽት ጽንፈኛ ሐይሎች ያላቸው ታጣቂዎቸ በወረዳው ከተማ ተኩስ ከፍቶ እንደነበር አረጋግጧል። ታጣቂዎቹ ጸረ ሽምቅ ተብሎ በሚጠሩ የጸጥታ ኃይሎች ከአካባቢው እንዲባረሩ መደረጋቸዉንም አመልክተዋል፡፡
ከወረዳው ዋና ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጫካ ሸሽቶ ቆይተዋል
ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አስተዳደር ዋና ከተማ ሻምቡ በ 47 ኪሜ ገደማ ርቀት ላይ በሚትገኘው የአቤዶንሮ ወረዳ ትናንት ምሽት ታጣቂዎች ወደ ወረዳው መግባታቸውን ተከትሎ ከ 3 ሺ በላይ ነዋሪዎች ወደ ጫካ መሸሻቸውን ያነጋርናቸው ነዋሪዎች አመልክተዋል። በወረዳው መሰል ጥቃቶች የተደጋገሙ ሲሆን ትናንት ምሽት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኃይል ቱሉ ዋዩ ወደ ተባለው የወረዳው ዋና ከተማ መግባታቸውን በአካባቢው ከሚገኙ ጸረ ሽምቅ ከተባሉ የመንግስት ጸጥታ ኃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ተገልጸዋል፡፡ ከከተማው ሸሽተው ከነበሩት ነዋሪ መካከል አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ነዋሪ ታጣቂዎቹ በአራት አቅጣጫ ወደ ከተማው መግባታቸውን አብራርተዋል፡፡
‹‹ ምሽት ላይ ወደ ከተማ ገብተው ከፍተኛ ተኩስ ነበር። በጸረ ሽምቅ ኃይልና ኦሮሚያ ፖሊስ ነው ትንሽ የተረጋጋው፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሀይል ነው ወደ ከተማ የገባው፡፡ ከ3፡30 ጀምሮ ለአንድ ሰዓት ያህል ተኩስ ነበር፡፡ ህዝቡ ቤቱን ለቆ ነው ወደ ጫካ የሸሸው፡፡ እኛ የነበርነበት ጫካ ወደ 3ሺ 40 የሚደርስ ሰው ነው የነበረው ዛሬ ረፋድ ላይ ወደ ከተማ ህዝቡ መመለስ ጀምሯል፡፡››
‹‹በወረዳው የሚደርሱ ጥቃቶች ለማስቀረት ትኩረት ተነፍገናል›› ነዋሪዎች
በነሐሴ ወር መጨረሻ በአካባቢው ሆማ ጋለሳ በተባለ ስፍራ በታጣቂዎች በርካቶች መገደላቸውን ተከትሎ የወረዳው አስተዳደር መሰል ጥቃቶችን ለመከላል በአካባቢው የጸጥታ ሐይል እየተጨመረ እንደሚገኝ ገልጾ ነበር፡፡ በትናንት ምሽት ጥቃት ሸሽተው ከነበሩት ሰዎች መካከል ያነጋርናቸው ሌላው ነዋሪም በወረዳው በታጣቂዎች ጥቃት ከ 2014 ዓ.ም ወዲህ በተደራጀ እና በተደጋጋሚ በቅርቡ ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በዚህ አካባቢ በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሱ የሚገኙ ጥቃቶች ትኩረት አለማግኘታቸን የተናገሩት ነዋሪው በርካቶች በስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ቦታ እንደሚሸሱ ገልጸዋል፡፡

‹‹ ከፍተኛ ኃይል እና ትጥቅ ያለው ሀይል ነው የገባው፡፡ ብሬንና ስናፔር የታጠቁ ናቸው፡፡ ምሽት ነው ወደ ከተማ ገብቶ ተኩስ የከፈቱትት፡፡ ህዝቡ እንዳለ በዝናብ ጫካ ነው ያደረሱት፡፡ ጉለንቴ፣ቱሉ ሞቲ እና ቱሉ መጢ በተባሉ ቦታዎች ታጣቂዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱበትና ጥቃት የሚፈጽሙባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡››
የአቤዶንጎሮ ወረዳ አስተዳደር በበኩሉ ጽንፈኛ ኃይሎች ያላቸው ታጣቂዎች ትናንት ምሽት ወደ ወረዳው ከተማ በመግባት ተኩስ መክፈታቸውን የገለጸ ሲሆን የደረሰውን የጉዳት መጠን ለጊዜው አልገለጹም፡፡ የወረዳው ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አለማየሁ ዱጉማ ታጣቂዎች ወደ ከተማ ገብቶ እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ያው ማታ ተኩስ ነበር እስካሁን የሆነ ነገር ለም እኛም ህብረተሰቡም ሰላም ነን›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በወረዳው በተለያየ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በሰዎች ላይ ጥቃት እንደሚያደርሱ ተገልጸዋል፡፡ በአቤዶንጎሮ ወረዳ ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም ከአጎራባች ስፍራዎቸ ተሻገሩ የተባሉ ታጠቂዎች ሆማ ጋለሳ በተባለ አንዱ የወረዳው ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት የበርታ ሰው ህይወት ማለፉ መዘገቡ ይታወሳል፡፡