የኢትዮጵያ የእዳ ጫና አስተማማኝ ደረጃ ላይ አይደለም ሲል ዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ባወጣው አዲስ ሪፖርት አስጠንቅቋል።
ተቋሙ፣ አገሪቱ ከፍተኛ እዳ እንደተጫናትና ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረትና የውጭ እዳ የመክፈል አቅም ውስንነት እንደገጠማት ገልጧል።
የአገሪቱ የውጭ እዳ ጫና ወሳኝ ደረጃዎችን ማለፉን፣ ከአጠቃላይ ዓመታዊ የአገሪቱ የወጪ ንግድ 206 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱንና አገሪቱ እዳዋን ለመክፈል የምታወጣው ወጪ በተያዘው ዓመት ከመንግሥት አጠቃላይ ገቢ 37 ነጥብ 7 በመቶውን እንደሚሸፍንም ተቋሙ ጠቅሷል።
ተቋሙ፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ ተጽዕኖዎች የመንግሥትን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሊያዘገዩት ወይም ሊቀለብሱት ይችላሉ በማለትም አስጠንቅቋል።