ብሪታንያ፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በገባችበት የባሕር በር ውጥረት ጋር በተያያዘ የተሳሳተ ስሌት እንዳትይዝ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴቪድ ላሚ ለኢትዮጵያ አቻቸው ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ባለፈው ነሃሴ ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር ሰጥተው እንደነበር የብሪታኒያ ፓርላማ አባላት ማክሰኞ’ላት ባደረጉት አንድ ውይይት ተገልጧል።
ላሚ ኢትዮጵያ ይልቁንም ውጥረቱን ለማርገብ ድርድርን እንድትመርጥ መምከራቸውን፣ በብሪታንያ ፓርላማ የመንግሥት ተጠሪ ጀራርድ ሌሞስ ፓርላማው በሁለቱ አገሮች ውጥረት ዙሪያ ባደረገው ውይይት ላይ ተናግረዋል። የብሪታንያ መንግሥት ለኤርትራ ባለስልጣናትም ተመሳሳይ መልዕክት አስተላልፏል ተብሏል።
ሌሞስ፣ ማንም አገር ለንግድ አገልግሎት የባሕር በር ማግኘት ያለበት በሰላማዊ ድርድር ብቻ ነው የሚል አቋም እንዳላትና በሌላ አገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ላይ የሚቃጣ የኃይል ዛቻ እንደማትደግፍ ተናግረዋል።
ብሪታንያ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለችና አገራቱ ውጥረቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ እያስጠነቀቀችና ድርድር እንዲጀምሩ ግፊት እያደረገች እንደሆነም ሌምስ ገልጸዋል።