በመስቀል አደባባይ በደረሰው የመደረክ መደርመስ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ታዳጊዎች አስከሬን ለዘመድ አዝማድ አይሰጥም በሚል ተከለከለ!

መረብ ሚዲያ አደጋው በደረሰ በደቂቃዎች ልዩነት የአይን እማኞችን አነጋግሮ በማህበራዊ ትስስር ገፆቹ መረጃውን ማስነበቡ አይዘነጋም።

ገዢው የብልፅግና ቡድን፡ የሕዳሴ ግድብ መመረቁን በማስመልከት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለዛሬ መስከረም 04/2018 ዓ/ም የድጋፍ ሰልፍ እንዲያካሂዱለት ባስተላለፈው መመሪያ መሠረት፡ በሰልፉ ላይ ልዩ ልዩ ትርኢቶችን እንዲያሳዩ ስልጠና ሲሰጣቸው የነበሩ ታዳጊዎች ተሰብስበውበት የነበረው መድረክ ተንዶ በበርካታ ታዳጊዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ማስከተሉን መረብ ሚዲያ ትናንት ምሽቱን የአይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ አደጋው በደረሰ በውስን ደቂቃዎች ልዩነት ዘግቦ ነበር።

አደጋው የደረሰው ትናንት መስከረም 03/2018 ዓ/ም ምሽት 2 ሰዓት ገደማ ላይ ሲሆን፡ አደጋው ከደረሰባቸው ታዳጊዎች መካከል ሕይወታቸው ያለፈ እንዳለ፡ ነገ ግን ብዛታቸውን በውል ማወቅ እንዳልተቻለ ምንጮቻችን በወቅቱ ገልፀው ነበረ።

መረብ ሚዲያ ያነጋገራቸው የአይን እማኞች፡ “እኛ በአከባቢው የነበርን ሰዎች ወደ ውስጥ ገብተን እንዳናግዝ ስለ ጉዳቱ መረጃ ታወጣላችሁ በሚል ተከልክለን፡ አከባቢው ከፍተኛ ቁጥር ባለው የፀጥታ ኃይል እየተጠበቀ ጥቂት የፖሊስ አባላት ብቻ ፍርስራሹን እንዲያነሱ ተደርጓል” ብለዋል።

ተጎጂዎቹን ከፍርስራሽ ውስጥ አውጥቶ ወደ ሕክምና ለመውሰድ ሰዓታትን ፈጅቷል ያሉት ምንጮቻችን፡ በዚህም መትረፍ የሚችሉ ታዳጊዎች አስቸኳይ እርዳታ ባለማገኘታቸው ሳይተርፉ ቀርተዋል ብለዋል።

በልጆቻቸው ላይ የደረሰውን አደጋ የሰሙ ወላጆች ተጎጂዎቹ ወደ ተወሰዱበት ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሄዱ ቢሆንም፡ ነገር ግን በሆስፒታሉ በር ላይ በቆሙ የፀጥታ ኃይሎች እንዳይገቡ ተከልክለዋል።

በዚህም በርካታ የተጎጂ ታዳጊዎች ቤተሰብ ለሊቱን ሙሉ በሆስፒታሉ በር ላይ ሆነው በለቅሶና ዋይታ ተሞልተው ማደራቸውን ጣቢያችን ለማረጋገጥ ችሏል።

የገዢው የብልፅግና ቡድን አመራሮች የሕዳሴ ግድብ መመረቁን በማስመልከት የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ የድጋፍ ሰልፍ እንዲያካሂድላቸው ለዛሬ መስከረም 04/2018 ዓ/ም ከጧት ጀምሮ በመስቀል አደባባይ ላዘጋጁት ፕሮግራም ልዩ ልዩ ትርኢቶችን እንዲያሳዩ በውጤታቸው የተሻሉ የተባሉ ዕድሜያቸው ከስምንት ዓመት ጀምሮ የሆኑ ታዳጊ ተማሪዎች ከየትምህርት ቤቱ ተመርጠው ስልጠና ሲሰጣቸው ሰንብቷል።

እነዚህ ታዳጊዎች ስልጠናው ሲሰጣቸው የሰነበተው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ቅጥር ጊቢ ሲሆን፡ ውሎና አዳራቸውም በዛው በካምፓሱ ውስጥ ሆኖ የአዲስ አመት በዓልን ጭምር ከቤተሰብ ጋር ሳይገናኙ በዛው እንዳሳለፉ ታውቋል።

ለዛሬ በነበረው የድጋፍ ሰልፍ፡ ፕሮግራሙ በሚካሄድበት በዛው በመስቀል አደባባይ የመጨረሻ ያሉትን የትርኢት ስልጠና ትናንት ምሽቱን ሲሰለጥኑ የነበሩት ታዳጊዎቹ፡ ተሰብስበውበት የነበረው መድረክ ተንዶ በበርካታ ታዳጊዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት አስከትሏል።

አደጋው የደረሰባቸው ልጆቻቸውን እንዳያዩ ተከልክለው የነበሩት ወላጆች ዛሬ ንጋት አከባቢ የተፈቀደላቸው ቢሆንም፡ ነገር ግን በርካታ ወላጆች የልጆቻቸውን እርብትብት የልጅ ትንፋሽን ሳይሆን በድን አካላቸውን ነው ያገኙት።

ሰማይ የተደፋባቸው ወላጆች የልጆቻቸውን አስከሬን ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ተላቅሰው እንዳይቀብሩ “ከበላይ አካላት የመጣ ትዕዛዝ ነው በሚል” አስከሬን እንዳይወስዱ ተከልክለዋል።

በተጨማሪም ሐዘንተኞቹ፡ “የድጋፍ ሰልፉን ገፅታ ያበላሻል ዛሬ ማልቀስ የለባችሁም” እንደተባሉም ተሰምቷል።

የብልፅግናው ሰዎች ስለጉዳዩ እንዳይሰማ እነሱ የሚዘውሯቸው ሚዲያዎችን ጨምሮ ለአክቲቪስቶቻቸው ጥብቅ መመሪያ ያስተላለፉ ሲሆን፡ ምንም ያልተፈጠረ በመምሰል መስቀል አደባባይ ላይ በደስታ ሲፍነሸነሹ ታይተዋል።

ማሳጂስቱ ዐብይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች የስርዓቱ ከፍተኛ አመራሮች የእነሱን ድግስ እንዲያሳምሩላቸው ተጠርተው ለዝግጅቱ ሲሰናዱ በሞቱትና በተጎዱ ታዳጊ ተማሪዎች የተሰማቸውን ሀዘን ሲገልፁ አልታዩም